የሉቃስ ወንጌል 23:50-56

የሉቃስ ወንጌል 23:50-56 አማ05

የአይሁድ ከተማ በሆነችው በአርማትያስ የሚኖር ዮሴፍ የሚባል ሰው ነበረ፤ እርሱ ጻድቅና ደግ ሰው ነበረ፤ የአይሁድ ሸንጎ አባልም ነበረ። ይሁን እንጂ በአይሁድ ምክርና ሤራ አልተባበረም፤ እርሱ የእግዚአብሔርን መንግሥት በተስፋ የሚጠባበቅ ሰው ነበረ። ይህ ሰው ወደ ጲላጦስ ፊት ቀርቦ የኢየሱስ አስከሬን እንዲሰጠው ጠየቀ። አስከሬኑንም አውርዶ በቀጭን ሐር ልብስ ከፈነው፤ ማንም ሰው ባልተቀበረበት ከአለት ተወቅሮ በተዘጋጀ መቃብር ውስጥ ቀበረው፤ ይህንንም ያደረገው ዓርብ ማታ ለሰንበት ዝግጅት በሚደረግበት ጊዜ ነበር። ኢየሱስን ተከትለው ከገሊላ የመጡ ሴቶች ከዮሴፍ ጋር ሄደው መቃብሩን አዩ፤ አስከሬኑም እንዴት እንደ ተቀበረ ተመለከቱ። ወደ ቤታቸውም ተመልሰው ለአስከሬን የሚሆኑ ጥሩ መዓዛ ያለው ቅመምና ሽቶ አዘጋጁ፤ በሕግ መሠረት በሰንበት ቀን ዐርፈው ዋሉ።