የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የሉቃስ ወንጌል 23:39-56

የሉቃስ ወንጌል 23:39-56 አማ05

ከኢየሱስ ጋር ከተሰቀሉት ወንጀለኞች አንዱ፥ ኢየሱስን፦ “አንተ መሲሕ አይደለህምን? እስቲ በል ራስህንና እኛን አድን!” እያለ ይሰድበው ነበር። ሌላው ወንጀለኛ ግን እንዲህ ብሎ ገሠጸው፦ “አንተ በተመሳሳይ ፍርድ ላይ እያለህ እግዚአብሔርን አትፈራምን? እኛ ባደረግነው በደል ምክንያት የሚገባንን ቅጣት አግኝተናል፤ ይህ ሰው ግን ምንም ጥፋት አላደረገም።” ቀጥሎም ኢየሱስን፦ “ጌታ ሆይ! በመንግሥትህ ስትመጣ አስታውሰኝ!” አለው። ኢየሱስም “በእውነት እልሃለሁ፤ ዛሬውኑ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ!” አለው። እነሆ፥ ይህ የሆነው ከቀኑ ስድስት ሰዓት ገደማ ነበር፤ ከዚያን ጊዜም ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ። ፀሐይ ጨለመ፤ የቤተ መቅደስ መጋረጃም ከመካከሉ ተቀዶ ከሁለት ተከፈለ። ኢየሱስም ድምፁን ከፍ አድርጎ፥ “አባት ሆይ! እነሆ! ነፍሴን በእጅህ ዐደራ እሰጣለሁ!” አለ፤ ይህንንም ካለ በኋላ ነፍሱ ከሥጋው ተለየች። በዚያ የነበረው መቶ አለቃ፥ የሆነውን ነገር ባየ ጊዜ፥ “በእርግጥ ይህ ሰው ጻድቅ ኖሮአል!” ብሎ እግዚአብሔርን አከበረ። ነገሩን ለመመልከት እዚያ ተሰብስበው የነበሩ ሰዎች ሁሉ የሆነውን ነገር ባዩ ጊዜ በማዘን ደረታቸውን እየመቱ ወደየቤታቸው ተመለሱ። ኢየሱስን በቅርብ ያውቁት የነበሩ ሰዎች ሁሉና ከገሊላ ጀምሮ ይከተሉት የነበሩ ሴቶችም በሩቅ ቆመው ይህን ነገር ይመለከቱ ነበር። የአይሁድ ከተማ በሆነችው በአርማትያስ የሚኖር ዮሴፍ የሚባል ሰው ነበረ፤ እርሱ ጻድቅና ደግ ሰው ነበረ፤ የአይሁድ ሸንጎ አባልም ነበረ። ይሁን እንጂ በአይሁድ ምክርና ሤራ አልተባበረም፤ እርሱ የእግዚአብሔርን መንግሥት በተስፋ የሚጠባበቅ ሰው ነበረ። ይህ ሰው ወደ ጲላጦስ ፊት ቀርቦ የኢየሱስ አስከሬን እንዲሰጠው ጠየቀ። አስከሬኑንም አውርዶ በቀጭን ሐር ልብስ ከፈነው፤ ማንም ሰው ባልተቀበረበት ከአለት ተወቅሮ በተዘጋጀ መቃብር ውስጥ ቀበረው፤ ይህንንም ያደረገው ዓርብ ማታ ለሰንበት ዝግጅት በሚደረግበት ጊዜ ነበር። ኢየሱስን ተከትለው ከገሊላ የመጡ ሴቶች ከዮሴፍ ጋር ሄደው መቃብሩን አዩ፤ አስከሬኑም እንዴት እንደ ተቀበረ ተመለከቱ። ወደ ቤታቸውም ተመልሰው ለአስከሬን የሚሆኑ ጥሩ መዓዛ ያለው ቅመምና ሽቶ አዘጋጁ፤ በሕግ መሠረት በሰንበት ቀን ዐርፈው ዋሉ።