የሉቃስ ወንጌል 22:7-23

የሉቃስ ወንጌል 22:7-23 አማ05

ከዚህ በኋላ የፋሲካ በግ የሚታረድበት የቂጣ በዓል ደረሰ። ኢየሱስ “የፋሲካውን ራት እንድንበላ ሄዳችሁ አዘጋጁልን” ሲል ጴጥሮስንና ዮሐንስን ላካቸው። እነርሱም “የፋሲካውን ራት የት እንድናዘጋጅ ትፈልጋለህ?” ሲሉ ጠየቁት። እርሱም እንዲህ አላቸው፦ “ወደ ከተማ ስትገቡ እነሆ፥ የውሃ እንስራ የተሸከመ ሰው ታገኛላችሁ፤ እርሱን ተከትላችሁ ወደሚገባበት ቤት ሂዱ። የቤቱንም ጌታ መምህራችን፥ ‘ከደቀ መዛሙርቴ ጋር የፋሲካን ራት የምበላበት የእንግዳ ማረፊያ ቤት የት ነው? ይልሃል’ በሉት። እርሱም በሰገነት ላይ ያለውን ተነጥፎ የተዘጋጀ ሰፊ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ በዚያ አዘጋጁ።” ሁለቱ ደቀ መዛሙርትም ሄደው፥ ሁሉ ነገር ልክ ኢየሱስ እንዳላቸው ሆኖ አገኙ፤ የፋሲካውንም ራት በዚያ አዘጋጁ። የእራት ሰዓት በደረሰ ጊዜ ኢየሱስ ከሐዋርያት ጋር በማእድ ተቀመጠ። እንዲህም አላቸው፤ “መከራ ከመቀበሌ በፊት ከእናንተ ጋር ይህን የፋሲካ ራት ለመብላት እጅግ እመኝ ነበር፤ የዚህ ነገር እውነተኛ ምሥጢር በእግዚአብሔር መንግሥት ፍጹም ሆኖ እስኪገለጥ ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ ይህን የፋሲካ ራት ከቶ አልበላም እላችኋለሁ።” ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ጽዋውን አንሥቶ ከአመሰገነ በኋላ እንዲህ አለ፦ “እንካችሁ ይህንን ተካፈሉ፤ በእውነት እላችኋለሁ ከአሁን ጀምሮ የእግዚአብሔር መንግሥት እስክትመጣ ድረስ ከዚህ ከወይን ፍሬ የሚገኘውን መጠጥ አልጠጣም።” ቀጥሎም ኢየሱስ ኅብስት አንሥቶ ከአመሰገነ በኋላ፤ ቈርሶ ለደቀ መዛሙርቱ “እንካችሁ፤ ይህ ለእናንተ የሚሰጥ ሥጋዬ ነው፤ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” ብሎ ሰጣቸው። እንዲሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን አንሥቶ ሰጣቸውና እንዲህ አላቸው፤ “ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው ደሜ የሚፈጸም አዲስ ኪዳን ነው። “ነገር ግን አሳልፎ የሚሰጠኝ ሰው እጅ እነሆ፥ ከእኔ ጋር በማእድ ነው። የሰው ልጅ ስለ እርሱ አስቀድሞ በተወሰነው መሠረት ይሞታል፤ ነገር ግን የሰውን ልጅ አሳልፎ ለሚሰጠው ለዚያ ሰው ወዮለት!” እነርሱም “ከእኛ መካከል ይህን ነገር የሚያደርግ የትኛው ነው?” በማለት እርስ በርሳቸው ተጠያየቁ።