የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የሉቃስ ወንጌል 22:35-53

የሉቃስ ወንጌል 22:35-53 አማ05

ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን፦ “የገንዘብ ቦርሳ፥ ከረጢት፥ ጫማም ሳትይዙ በላክኋችሁ ጊዜ የጐደለባችሁ ነገር ነበርን?” አላቸው። እነርሱም “ምንም የጐደለብን ነገር አልነበረም” ሲሉ መለሱለት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “አሁን ግን የገንዘብ ቦርሳም ሆነ ከረጢት ያለው ይያዝ፤ ሰይፍም የሌለው ልብሱን ሸጦ ሰይፍ ይግዛ። ስለ እኔ አስቀድሞ የተጻፈው ሁሉ መፈጸም ስለሚገባው ‘ከዐመፀኞች ጋር ተቈጠረ’ የሚለው የቅዱስ መጽሐፍ ቃል በእኔ ላይ መፈጸም አለበት እላችኋለሁ።” ደቀ መዛሙርቱም “ጌታ ሆይ! እነሆ፥ እዚህ ሁለት ሰይፎች አሉ!” አሉት። እርሱም “ይበቃል!” አላቸው። ኢየሱስ ከከተማ ወጥቶ እንደ ልማዱ ወደ ደብረ ዘይት ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም አብረውት ሄዱ። እዚያም በደረሱ ጊዜ ኢየሱስ፦ “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ጸልዩ” አላቸው። 41 ከዚህ በኋላ የድንጋይ ውርወራ ያኽል ከእነርሱ ራቅ ብሎ ሄደ፤ ተንበርክኮም እንዲህ ሲል ጸለየ፦ “አባት ሆይ! ፈቃድህ ቢሆን ይህን የመከራ ጽዋ ከእኔ አርቅልኝ፤ ግን የአንተ ፈቃድ ይሁን እንጂ የእኔ ፈቃድ አይሁን።” በዚያን ጊዜ የሚያበረታታው መልአክ ከሰማይ መጥቶ ታየው። ልቡም በጣም ተጨንቆ በብርቱ ይጸልይ ነበር፤ ላቡም እንደ ደም ሆኖ ወደ መሬት ይንጠባጠብ ነበር። ከጸሎቱ ተነሥቶ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጣ፤ ከሐዘን ብዛት የተነሣ ተኝተው አገኛቸውና እንዲህ አላቸው፤ “ስለምን ትተኛላችሁ? ይልቅስ ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተነሡና ጸልዩ።” ኢየሱስ ይህን ሲናገር ሳለ እነሆ፥ ብዙ ሰዎች መጡ፤ መሪያቸው ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው ይሁዳ ነበር፤ ይሁዳ ሊስመው ወደ ኢየሱስ ቀረበ። ኢየሱስ ግን “ይሁዳ ሆይ! የሰውን ልጅ በመሳም አሳልፈህ ትሰጣለህን?” አለው። ከኢየሱስ ጋር የነበሩት ደቀ መዛሙርት የነገሩን ሁኔታ ባዩ ጊዜ “ጌታ ሆይ! በሰይፍ እንምታቸውን?” አሉ። ከእነርሱም አንዱ የካህናት አለቃውን አገልጋይ በሰይፍ መታና ቀኝ ጆሮውን ቈረጠ። ኢየሱስ ግን “ተው! እንደዚህ ያለ ነገር ደግመህ አታድርግ!” አለ፤ የሰውዬውንም ጆሮ ዳስሶ አዳነው። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ሊይዙት የመጡትን የካህናት አለቆች፥ የቤተ መቅደስ የዘብ አዛዦችንና የሕዝብ ሽማግሌዎችንም እንዲህ አላቸው፦ “እኔን እንደ ወንበዴ ልትይዙ ሰይፍና ዱላ ይዛችሁ መጣችሁን? በየቀኑ በቤተ መቅደስ ከእናንተ ጋር ስገኝ አልያዛችሁኝም ነበር፤ አሁን ግን የእናንተ ጊዜና የጨለማው ሥልጣን ጊዜ ነው።”