የሉቃስ ወንጌል 19:11-27

የሉቃስ ወንጌል 19:11-27 አማ05

ሰዎቹ ይህን በመስማት ላይ ሳሉ ኢየሱስ አንድ ምሳሌ ደግሞ ነገራቸው፤ እርሱ ወደ ኢየሩሳሌም ስለ ተቃረበ ሰዎቹ የእግዚአብሔር መንግሥት አሁኑኑ የምትገለጥ መስሎአቸው ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “የንጉሥነትን ሥልጣን ተቀብሎ ለመመለስ ወደ ሩቅ አገር የሄደ አንድ መኰንን ነበረ፤ እርሱ ከመሄዱ በፊት ከአገልጋዮቹ ዐሥሩን ጠርቶ ለእያንዳንዱ ዐሥር ምናን ሰጣቸውና ‘ተመልሼ እስክመጣ ድረስ በዚህ ገንዘብ ነግዱ’ አላቸው። የአገሩ ሰዎች ግን ይጠሉት ስለ ነበር፥ ይህ ሰው በእኛ ላይ እንዲነግሥ አንፈልግም ሲሉ እርሱ ከሄደ በኋላ መልእክተኛ ላኩ። “ያ ሰው ንጉሥ ሆኖ በተመለሰ ጊዜ በተሰጣቸው ገንዘብ ነግደው ምን ያኽል እንዳተረፉ ለማወቅ፥ ገንዘብ ሰጥቶአቸው የነበሩትን አገልጋዮቹን አስጠራቸው። የመጀመሪያው አገልጋይ ቀርቦ፦ ‘ጌታ ሆይ! የሰጠኸኝ አንድ ምናን እነሆ፥ ዐሥር ምናን አትርፎአል’ አለው። ጌታውም ‘አንተ መልካም አገልጋይ! ደግ አደረግህ፤ በትንሽ ነገር ስለ ታመንህ እኔ ደግሞ በዐሥር ከተሞች ላይ ሥልጣን ሰጥቼሃለሁ’ አለው። ሁለተኛውም አገልጋይ ቀርቦ ‘ጌታ ሆይ! የሰጠኸኝ ምናን እነሆ! አምስት ምናን አትርፎአል’ አለው። ጌታውም ይህኛውን ‘አንተንም ደግሞ በአምስት ከተሞች ላይ ሾሜሃለሁ’ አለው። “ሌላውም አገልጋይ ቀርቦ እንዲህ አለ፤ ‘ጌታዬ ሆይ! የሰጠኸኝ ገንዘብ ይኸውልህ፤ በጨርቅ ቋጥሬ አስቀምጬው ነበር። ይህንንም ያደረግኹት አንተ ያላስቀመጥከውን የምትወስድ፥ ያልዘራኸውንም የምትሰበስብ፥ ኀይለኛ ሰው መሆንህን ዐውቄ ስለ ፈራሁህ ነው’ አለው። ጌታውም ‘አንተ መጥፎ አገልጋይ! በአነጋገርህ እፈርድብሃለሁ፤ እኔ ያላስቀመጥኩትን የምወስድና ያልዘራሁትን የምሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆኔን ዐውቀሃል፤ ታዲያ ገንዘቤን ትርፍ በሚያስገኝልኝ በባንክ ለምን አላስቀመጥከውም ነበር? እኔ ተመልሼ ስመጣ ከነትርፉ እወስደው ነበር’ አለው። ከዚህ በኋላ ጌትዮው፥ በዚያ ቆመው የነበሩትን፦ ‘ምናኑን ከእርሱ ወስዳችሁ ዐሥር ምናን ላለው አገልጋይ ስጡት’ አላቸው። እነርሱም ‘ጌታ ሆይ! እርሱ እኮ ዐሥር ምናን አለው!’ አሉት። ጌትዮውም ‘ላለው ሁሉ ይበልጥ ይሰጠዋል፤ ከሌለው ሰው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል እላችኋለሁ። በእነርሱ ላይ እንድነግሥ ያልፈለጉትን እነዚያን ጠላቶቼን ግን እዚህ አምጥታችሁ በፊቴ ግደሉአቸው!’ ” አላቸው።