የሉቃስ ወንጌል 17:1-19

የሉቃስ ወንጌል 17:1-19 አማ05

ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ፦ “ሰዎችን አሰናክለው ወደ ኃጢአት የሚጥሉ ነገሮች መምጣታቸው አይቀርም፤ ነገር ግን የኃጢአትን መሰናክል ለሚያመጣው ለዚያ ሰው ወዮለት! ማንም ሰው ከእነዚህ ታናናሾች አንዱን ከሚያሰናክል ይልቅ ትልቅ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ላይ ታስሮ ወደ ባሕር ቢጣል ይሻለው ነበር። ስለዚህ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ! ወንድምህ ቢበድልህ ገሥጸው! በበደሉ ከተጸጸተም ይቅር በለው! በቀን ሰባት ጊዜ ቢበድልህና በቀን ሰባት ጊዜም ወደ አንተ እየመጣ ‘በበደሌ ተጸጽቼአለሁ’ ቢልህ ይቅር በለው።” ሐዋርያቱም ጌታ ኢየሱስን “እባክህ እምነት ጨምርልን” አሉት። ጌታ ኢየሱስም “የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያኽል እምነት ቢኖራችሁ ይህን የሾላ ዛፍ ‘ከዚህ ተነቅለህ በባሕር ውስጥ ተተከል!’ ብትሉት ይታዘዝላችኋል” አላቸው። ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “ከእናንተ አንዱ በእርሻ ሥራ የተሰማራ፥ ወይም በጎች የሚጠብቅ አገልጋይ ቢኖረው፥ አገልጋዩ ከሥራው በተመለሰ ጊዜ ወዲያውኑ ‘ና ተቀመጥና ራትህን ብላ’ ይለዋልን? ይልቅስ፥ ‘በል! ራቴን አዘጋጅልኝ፤ እስክበላና እስክጠጣም አደግድገህ አገልግለኝ፤ ከዚህ በኋላ አንተ ደግሞ ትበላለህ፥ ትጠጣለህ’ ይለው የለምን? ታዲያ፥ አገልጋዩ የታዘዘውን ስለ ፈጸመ ጌታው የሚያመሰግነው ይመስላችኋልን? እናንተም እንዲሁ የታዘዛችሁትን ሁሉ በፈጸማችሁ ጊዜ፥ ‘የማንጠቅም አገልጋዮች ነን፤ የፈጸምነውም ግዳጃችንን ብቻ ነው’ በሉ።” ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ በሰማርያና በገሊላ መካከል ያልፍ ነበር፤ ወደ አንዲት መንደርም በገባ ጊዜ ዐሥር ለምጻሞች ወደ እርሱ መጥተው በሩቅ ቆሙ፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው “ኢየሱስ ሆይ፥ መምህር ሆይ፥ እባክህ ማረን!” እያሉ ጮኹ። ኢየሱስም አያቸውና “ሂዱ! ሰውነታችሁን ለካህናት አሳዩ!” አላቸው፤ እነርሱም በመሄድ ላይ ሳሉ ከለምጻቸው ነጹ። ከእነርሱም አንዱ ከለምጹ መንጻቱን ባየ ጊዜ በከፍተኛ ድምፅ እግዚአብሔርን እያመሰገነ ተመለሰ። ኢየሱስንም እያመሰገነ በእግሩ ሥር በግምባሩ ተደፋ፤ እርሱ የሰማርያ ሰው ነበር። ኢየሱስም እንዲህ አለ፤ “ከለምጽ የነጹት ሰዎች ዐሥር አልነበሩምን? ታዲያ፥ ዘጠኙ የት አሉ? እግዚአብሔርን ለማመስገን ተመልሶ የመጣ ከዚህ ከባዕድ ሰው በቀር ሌላ አንድም አልተገኘምን?” ከዚህም በኋላ ኢየሱስ ያን ሰው፦ “ተነሥና ሂድ፤ እምነትህ አድኖሃል” አለው።