በዚያን ጊዜ ሰዎች ወደ ኢየሱስ መጥተው፥ “የገሊላ ሰዎች መሥዋዕት በሚያቀርቡበት ጊዜ ጲላጦስ ገደላቸው፤ ደማቸውም ከመሥዋዕታቸው ጋር አደባለቀ” ሲሉ ነገሩት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ታዲያ፥ እነዚህ የገሊላ ሰዎች ይህ ጥፋት የደረሰባቸው ከሌሎቹ የገሊላ ሰዎች ሁሉ ይበልጥ ኃጢአተኞች ስለ ነበሩ ይመስላችኋልን? ‘አይደለም፤ ንስሓ ባትገቡ እናንተም እንደእነርሱ ትጠፋላችሁ’ እላችኋለሁ። በሰሊሆም ግንብ ተደርምሶባቸው ስለሞቱት ዐሥራ ስምንት ሰዎች ምን ታስባላችሁ? እነርሱ በኢየሩሳሌም ከሚኖሩት ሰዎች ሁሉ የባሱ ኃጢአተኞች የነበሩ ይመስሉአችኋልን? አይደለም! ንስሓ ባትገቡ እናንተም እንደእነርሱ ትጠፋላችሁ እላችኋለሁ።” ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፦ “አንድ ሰው በወይን ተክሉ ቦታ ውስጥ የተተከለች አንዲት የበለስ ዛፍ ነበረችው፤ ከዚያች የበለስ ዛፍ ፍሬ አገኛለሁ ብሎ ቢሄድ ምንም ሳያገኝ ቀረ። ስለዚህ አትክልተኛውን ‘እነሆ፥ ከዚህች የበለስ ዛፍ ፍሬ ለማግኘት ሦስት ዓመት ሙሉ ተመላለስኩ፤ ግን ምንም ፍሬ አላገኘሁባትም፤ አሁንስ ቊረጣት! ስለምንስ መሬቱን ታበላሻለች?’ አለው። አትክልተኛው ግን እንዲህ ሲል መለሰለት፤ ‘ጌታዬ ሆይ! እስቲ ለዚህ ዓመት ደግሞ ተዋት፤ ዙሪያዋን ኰትኲቼ ማዳበሪያ አደርግላታለሁ፤ ለመጪው ዓመት ፍሬ ብትሰጥ መልካም ነው፤ አለበለዚያ ግን ትቈረጣለች።’ ” ኢየሱስ በሰንበት ቀን ከምኲራቦቹ በአንዱ ያስተምር ነበር፤ ከዚያም ከዐሥራ ስምንት ዓመት ጀምሮ ርኩስ መንፈስ ጀርባዋን ያጐበጣት አንዲት ሴት ነበረች፤ እርስዋ ወገብዋ በመጒበጡ ቀና ለማለት በፍጹም አትችልም ነበር። ኢየሱስ ባያት ጊዜ ጠራትና “አንቺ ሴት ከበሽታሽ ተፈውሰሻል!” አላት። እጆቹን ጫነባት፤ ወዲያውም ቀጥ ብላ ቆመች፤ እግዚአብሔርንም አመሰገነች። ኢየሱስ በሰንበት ቀን ስለ ፈወሰ የምኲራቡ አለቃ ተቈጣና ለሕዝቡ፦ “በሳምንት ውስጥ ሥራ የሚሠራባቸው ስድስት ቀኖች አሉ፤ በእነዚህ ቀኖች እየመጣችሁ ተፈወሱ፤ በሰንበት ቀን ግን አይሆንም” ብሎ ተናገረ። ጌታ ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “እናንተ ግብዞች፥ ከእናንተስ እያንዳንዱ በሰንበት ቀን በሬውን ከተዘጋበት አውጥቶ፥ ወይም አህያውን ከታሰረበት ፈቶ ውሃ ወደሚያጠጣበት ቦታ ይወስደው የለምን? እነሆ፥ የአብርሃም ዘር የሆነች ይህች ሴት ዐሥራ ስምንት ዓመት ሙሉ በሰይጣን ታስራ ስትሠቃይ ኖራለች፤ ታዲያ፥ እርስዋ ታስራ ከምትሠቃይበት በሽታ በሰንበት ቀን መፈታት አይገባትምን?” በዚህም ንግግሩ ኢየሱስ ተቃዋሚዎቹን ሁሉ አሳፈራቸው፤ ሕዝቡ ግን ኢየሱስ ባደረገው ድንቅ ነገር ሁሉ ተደሰተ። ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔር መንግሥት በምን ትመሰላለች? ወይስ ከምን ጋር አነጻጽራታለሁ? አንድ ሰው በአትክልቱ ውስጥ የዘራትን የሰናፍጭ ዘር ትመስላለች፤ እርስዋ አድጋ ዛፍ ሆነች፤ ወፎችም በቅርንጫፎችዋ ላይ ጎጆአቸውን ሠሩ።” ኢየሱስ እንደገና እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔርን መንግሥት ከምን ጋር አነጻጽራታለሁ? የእግዚአብሔር መንግሥት፥ አንዲት ሴት ሊጡ በሙሉ እንዲቦካ በሦስት መስፈሪያ ዱቄት ውስጥ የለወሰችውን እርሾ ትመስላለች።”
የሉቃስ ወንጌል 13 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሉቃስ ወንጌል 13:1-21
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች