ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ባጭር ታጥቃችሁ ሁልጊዜ ለሥራ ተዘጋጁ፤ መብራታችሁም የበራ ይሁን። በዚህም አኳኋን፥ ጌታቸው ከሠርግ ቤት መመለሱን የሚጠባበቁ አገልጋዮችን ምሰሉ፤ እነርሱ ጌታቸው በድንገት መጥቶ በሩን በሚያንኳኳበት ጊዜ ፈጥነው ለመክፈት ዝግጁዎች ናቸው። እነዚያ ጌታቸው ድንገት በመጣ ጊዜ፥ ነቅተው ሲጠብቁ የሚያገኛቸው አገልጋዮች እንዴት የተመሰገኑ ናቸው? በእውነት እላችኋለሁ፤ እርሱ ባጭር ታጥቆ በማእድ ያስቀምጣቸዋል፤ ቀርቦም ያገለግላቸዋል። ጌታቸው በእኩለ ሌሊት ወይም ከእኩለሌሊት በኋላ በመጣ ጊዜ ነቅተውና ተግተው ሲጠብቁት የሚያገኛቸው አገልጋዮች የተባረኩ ናቸው። ደግሞም ይህን ዕወቁ፤ አንድ ሰው ሌባ የሚመጣበትን ሰዓት ቢያውቅ ኖሮ ሌባው ቤቱን ቆፍሮ እንዲገባ አይተወውም ነበር። የሰው ልጅም ባላሰባችሁበት ሰዓት በድንገት ይመጣል፤ ስለዚህ እናንተም ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ።” ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ! ይህን ምሳሌ የምትናገረው ለእኛ ብቻ ነውን? ወይስ ለሁሉም ነው?” ሲል ኢየሱስን ጠየቀው። ጌታ ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ታዲያ ቤተሰቦቹን በደንብ እንዲያስተዳድርለትና ለአገልጋዮቹም ምግባቸውን በተመደበው ጊዜ እንዲሰጣቸው ጌታው የሚሾመው ታማኝና ብልኅ መጋቢ ማን ነው? ጌታው ከሄደበት ሲመለስ ልክ እንደታዘዘው ሲፈጽም የሚያገኘው አገልጋይ እንዴት የተባረከ ነው! በእውነት እላችኋለሁ፤ ጌታው ያን አገልጋይ የንብረቱ ሁሉ ኀላፊ አድርጎ ይሾመዋል። ነገር ግን ያ አገልጋይ ‘ጌታዬ ቶሎ አይመጣም፤ ይዘገያል’ ብሎ በማሰብ እየበላ፥ እየጠጣ፥ እየሰከረም ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮችን መምታት ይጀምራል። ይሁን እንጂ ጌታው ባልታሰበበት ቀንና ባልተጠበቀበት ሰዓት በድንገት ይመጣል፤ አገልጋዩንም በብርቱ ይቀጣዋል፤ ዕድሉንም ከወስላቶች ጋር እንዲሆን ያደርጋል። “የጌታውን ፈቃድ እያወቀ ያልተዘጋጀ፥ ወይም የጌታውን ትእዛዝ ያልፈጸመ አገልጋይ በብርቱ ይቀጣል። ነገር ግን የጌታውን ፈቃድ ባለማወቅ፥ ቅጣት የሚያመጣበትን ነገር አድርጎ ቢገኝ ቅጣቱ ይቀልለታል፤ ብዙ ከተሰጠው ሰው ብዙ ይፈለግበታል፤ ብዙ ዐደራም ከተሰጠው ሰው፥ ብዙ ይጠበቅበታል።”
የሉቃስ ወንጌል 12 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሉቃስ ወንጌል 12:35-48
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች