ሄሮድስ በይሁዳ ምድር ንጉሥ በነበረበት ዘመን፥ ከአብያ የክህነት አገልግሎት ክፍል የሆነ ዘካርያስ የሚባል ካህን ነበር። እርሱም ከአሮን ዘር የምትወለድ ኤልሳቤጥ የምትባል ሚስት ነበረችው። ሁለቱም በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ፤ የጌታንም ትእዛዝና ሥርዓት ያለ ነቀፋ ይጠብቁ ነበር። ኤልሳቤጥ መኻን ስለ ነበረች ልጅ አልነበራቸውም፤ ደግሞ ሁለቱም በጣም አርጅተው ነበር። በዚያን ጊዜ የዘካርያስ የክህነት ቡድን ለቤተ መቅደስ አገልግሎት ተረኛ ነበር፤ ስለዚህ እርሱ በእግዚአብሔር ፊት የክህነቱን አገልግሎት በመፈጸም ላይ ነበር። እንደ ካህናት አሠራር ልማድ ወደ ጌታ ቤተ መቅደስ ገብቶ ዕጣን ለማጠን ዕጣ ደረሰው። በቤተ መቅደሱም ውስጥ ዕጣን በሚታጠንበት ጊዜ፥ ሕዝቡ ሁሉ በውጪ ቆመው ይጸልዩ ነበር። የጌታ መልአክ ዕጣን በሚጤስበት መሠዊያ በስተቀኝ በኩል ቆሞ ለዘካርያስ ታየው። ዘካርያስ መልአኩን ባየው ጊዜ ደንግጦ በፍርሃት ተዋጠ። መልአኩ ግን እንዲህ አለው፦ “ዘካርያስ ሆይ! አትፍራ! ጸሎትህ ተሰምቶልሃል፤ ሚስትህ ኤልሳቤጥ ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ዮሐንስ ብለህ ትጠራዋለህ። የእርሱ መወለድ ለአንተ ተድላና ደስታ ይሆንልሃል፤ ብዙዎችም በመወለዱ እንዲሁ ደስ ይላቸዋል። እርሱ በጌታ ፊት ታላቅ ይሆናል፤ የወይን ጠጅና ሌላም የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣም፤ ገና በእናቱ ማሕፀን ሳለ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ይሆናል። እርሱ ከእስራኤል ሕዝብ ብዙዎቹን ወደ ጌታ ወደ አምላካቸው ይመልሳቸዋል፤ ልክ እንደ ነቢዩ ኤልያስ በመንፈስና በኀይል ሆኖ እርሱ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆቻቸው፥ የማይታዘዙትንም ሰዎች ልብ ወደ ጻድቃን ጥበብ ይመልሳል፤ ሕዝቡንም በማንቃት ለጌታ እንዲዘጋጅ ያደርጋል።” ዘካርያስ ግን መልአኩን “ይህ ነገር እርግጥ መሆኑን በምን ዐውቃለሁ? እኔ አርጅቻለሁ፤ ሚስቴም በዕድሜዋ ገፍታለች” አለው። መልአኩም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፤ ይህን የምሥራች እንድነግርህ ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኬ መጥቻለሁ። አንተ ግን ጊዜው ሲደርስ የሚፈጸመውን ቃሌን አላመንክም፤ ስለዚህ ይህ የነገርኩህ ሁሉ እስከሚፈጸም ድረስ ድዳ ትሆናለህ፤ መናገርም አትችልም።” በዚህ ጊዜ ሰዎቹ ዘካርያስን ይጠባበቁ ነበር፤ በቤተ መቅደስ ውስጥ ስለ ዘገየባቸውም ተገረሙ። ዘካርያስ ከቤተ መቅደስ በወጣ ጊዜ ከሰዎቹ ጋር መነጋገር አልቻለም፤ ስለዚህ እነርሱ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ራእይ የታየው መሆኑን ዐወቁ፤ እርሱ በእጁ እየጠቀሰ ያስረዳቸው ነበር። በዚህም ሁኔታ ዱዳ ሆኖ ቈየ። የአገልግሎቱም ጊዜ ከተፈጸመ በኋላ ዘካርያስ ወደ ቤቱ ሄደ።
የሉቃስ ወንጌል 1 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሉቃስ ወንጌል 1:5-23
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos