የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የሉቃስ ወንጌል 1:39-80

የሉቃስ ወንጌል 1:39-80 አማ05

በዚያን ጊዜ ማርያም በተራራማው በይሁዳ አገር ወዳለችው ከተማ በፍጥነት ተነሥታ ሄደች። ወደ ዘካርያስ ቤትም ገብታ ለኤልሳቤጥ ሰላምታ ሰጠቻት። ኤልሳቤጥ የማርያምን የሰላምታ ቃል በሰማች ጊዜ በማሕፀንዋ የነበረው ሕፃን ዘለለ። ኤልሳቤጥም በመንፈስ ቅዱስ ተሞልታ፥ ድምፅዋንም ከፍ አድርጋ እንዲህ አለች፦ “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፤ ከአንቺ የሚወለደውም የተባረከ ነው። የጌታዬ እናት ልትጐበኘኝ መምጣትዋ ለእኔ እንዴት ያለ ታላቅ ክብር ነው፤ ገና የሰላምታሽን ድምፅ ከመስማቴ በማሕፀኔ ያለው ሕፃን በደስታ ዘለለ። አንቺ ጌታ የተናገረውን ሁሉ የሚፈጽም መሆኑን በማመንሽ ምንኛ የተባረክሽ ነሽ!” ማርያምም እንዲህ አለች፦ “ነፍሴ ጌታን ታመሰግናለች፤ መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ትደሰታለች፤ እግዚአብሔር እኔን ዝቅተኛ አገልጋይቱን ተመልክቶአልና፥ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ የተባረክሽ ነሽ ይሉኛል፤ ኀያሉ እግዚአብሔር ታላላቅ ነገሮችን አድርጎልኛልና። ስሙም ቅዱስ ነው። እግዚአብሔር ለሚፈሩት ሰዎች ሁሉ ከትውልድ እስከ ትውልድ ምሕረቱን ያደርጋል። በብርቱ ክንዱ ኀይሉን አሳይቶአል፤ ትዕቢተኞችንም ከነሐሳባቸው በትኖአቸዋል። ታላላቅ ገዢዎችን ከዙፋናቸው አውርዶአቸዋል፤ ዝቅተኞችን ግን በክብር ከፍ አድርጎአቸዋል። የተራቡትን በመልካም ነገር አጥግቦአቸዋል፤ ሀብታሞችን ግን ባዶ እጃቸውን ሰዶአቸዋል፤ ለአብርሃምና ለዘሩ ለዘለዓለም ያሳየውን ምሕረት በማስታወስ፥ አገልጋዩን እስራኤልን ረድቶታል። ይህንንም ያደረገው ለቀድሞ አባቶቻችን የሰጠውን የተስፋ ቃል ለመፈጸም ነው።” ማርያምም ከኤልሳቤጥ ጋር ሦስት ወር ያኽል ከቈየች በኋላ ወደ ቤትዋ ተመልሳ ሄደች። ኤልሳቤጥ የመውለጃዋ ጊዜ ደረሰና ወንድ ልጅ ወለደች። ጐረቤቶችዋና ዘመዶችዋ ሁሉ ጌታ ታላቅ ምሕረቱን እንዳደረገላት ሰምተው ከእርስዋ ጋር ተደሰቱ። ሕፃኑ በተወለደ በስምንተኛው ቀን፥ በግዝረቱ ሥነ ሥርዓት ላይ ለመገኘት ጐረቤቶችዋና ዘመዶችዋ ተሰብስበው መጡ፤ ባባቱ ስም ዘካርያስ ብለው ሊጠሩት ፈልገው ነበር፤ እናቱ ግን “እንዲህ አይሆንም፤ ስሙ ዮሐንስ ነው” አለች። እነርሱም “ከዘመዶችሽ በዚህ ስም የተጠራ ማንም የለም?” አሉአት። ከዚህም በኋላ አባቱን፦ “ልጅህ ማን ተብሎ እንዲጠራ ትፈልጋለህ?” ብለው በምልክት ጠየቁት። ዘካርያስም መጻፊያ እንዲሰጡት ጠይቆ፦ “ስሙ ዮሐንስ ነው” ብሎ ጻፈ፤ ሁሉም በዚህ ነገር ተደነቁ። በዚያኑ ጊዜ ዘካርያስ አንደበቱ ተፈቶለት መናገር ቻለ፤ እግዚአብሔርንም ማመስገን ጀመረ። ከዚህም የተነሣ በጐረቤቶቻቸው ሁሉ ፍርሀት አደረባቸው፤ ዜናውም በተራራማው በይሁዳ ምድር ሁሉ ተሰማ። ይህን ነገር የሰሙ ሁሉ፥ “ይህ ሕፃን ምን ሊሆን ይሆን?” እያሉ ይጠያየቁ ነበር። ይህም የሆነው የእግዚአብሔር ረድኤት በእርግጥ ከእርሱ ጋር ስለ ነበር ነው። የሕፃኑ አባት ዘካርያስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ እንዲህ ሲል ትንቢት ተናገረ፦ “ሕዝቡን በምሕረት ስለ ጐበኘና ስላዳነ፥ የእስራኤል አምላክ፥ ጌታ ይመስገን! ከአገልጋዩ ከዳዊት ዘር ኀያል አዳኝ አስነሥቶልናል፤ ከጥንት ዘመን ጀምሮ በነበሩት በቅዱሳን ነቢያቱ አፍ እንደ ተናገረ፤ ከጠላቶቻችንና ከባላጋራዎቻችን እጅ አድኖናል፤ ይህንንም ማድረጉ ለአባቶቻችን ምሕረትን እንደሚያደርግና የተናገረውንም ቅዱስ ቃል ኪዳኑን እንደሚፈጽም በማሰብ ነው። ይህንንም ቃል ኪዳን፥ በመሐላ የሰጠው ለአባታችን ለአብርሃም ነበር፤ የተስፋውም ቃል ከጠላቶቻችን እጅ ነጻ ወጥተን፥ ያለ ፍርሀት እንድናገለግለው ነው፤ እንዲሁም በሕይወታችን ዘመን ሁሉ፥ በእግዚአብሔር ፊት በቅድስናና በጽድቅ መኖር እንድንችል ነው። ደግሞም አንተ ሕፃን፥ የልዑል እግዚአብሔር ነቢይ ትባላለህ። መንገዱን ለማዘጋጀት ቀድመህ በጌታ ፊት ትሄዳለህ። ጌታም ኃጢአታቸውን ይቅር በማለት የመዳንን ዕውቀት ይሰጣቸዋል። አምላካችን መሓሪና ርኅሩኅ በመሆኑ የደኅንነት ብርሃን ከወደላይ እንዲበራልን ያደርጋል። እርሱ በጨለማና በሞት ጥላ ሥር ላሉት ሁሉ ያበራል፤ እርምጃችንንም ወደ ሰላም መንገድ ይመራል።” ሕፃኑም አደገ፤ በመንፈስም ጠነከረ፤ ለእስራኤል ሕዝብ እስከ ታየበት ጊዜ ድረስ በበረሓ ኖረ።

Free Reading Plans and Devotionals related to የሉቃስ ወንጌል 1:39-80