የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘሌዋውያን 7:1-10

ኦሪት ዘሌዋውያን 7:1-10 አማ05

“እጅግ የተቀደሰ ስለ ሆነው የበደል ስርየት መሥዋዕት አቀራረብ የተሰጠው መመሪያ ይህ ነው፤ መሥዋዕት ሆኖ የቀረበው እንስሳ፥ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርቡት እንስሶች በሚታረዱበት ስፍራ ይታረድ፤ ደሙም በመሠዊያው ጐን በአራቱም ማእዘን ይረጭ። ስቡ ሁሉ ተገፎ፥ ይኸውም የላቱ ስብ፥ የሆድ ዕቃውን የሚሸፍነው ስብ፥ ኲላሊቶቹና በእነርሱ ላይ የሚገኘው ስብ፥ እንዲሁም እንደ መረብ ሆኖ ጉበቱን ከሚሸፍነው ስብ ምርጥ የሆነው ክፍል ተወስዶ በመሠዊያው ላይ መሥዋዕት ሆኖ ይቅረብ፤ በመሠዊያውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ ካህኑ ለእግዚአብሔር መባ አድርጎ በእሳት ያቃጥለው፤ ይህም የበደል መሥዋዕት ነው። ከካህናት ወገን የሆነ ወንድ ሁሉ የመሥዋዕቱን ሥጋ ይብላ፤ ነገር ግን ያ መሥዋዕት እጅግ የተቀደሰ ስለ ሆነ በተቀደሰ ስፍራ ይብላው። “ስለ ኃጢአት ስርየት በሚቀርበው መሥዋዕትና ስለ በደል ስርየት በሚቀርበው መሥዋዕት መካከል ለሁለቱም የሚሠራ አንድ ዐይነት ሕግ አለ፤ ይኸውም የእንስሳው ሥጋ መሥዋዕቱን ለሚያቀርበው ካህን ምግብ እንዲሆን ይሰጣል፤ ለሚቃጠል መሥዋዕት የቀረበው እንስሳ፥ ቆዳው ተገፎ መሥዋዕቱን ላቀረበው ካህን ይሰጠዋል፤ በእቶን የተጋገረው የእህል መባ ሁሉ፥ ወይም በመቀቀያ የበሰለውና በምጣድ የተጋገረው መሥዋዕት አድርጎ ላቀረበው ካህን ይሰጣል፤ በዘይት የተለወሰም ቢሆን ወይም ደረቅ ያልበሰለው የእህል መባ ግን ትውልዳቸው ከአሮን ወገን ለሆነው ካህናት ሁሉ ይሰጥ፤ እርሱንም እኩል ይካፈሉት።