ኦሪት ዘሌዋውያን 11
11
የሚበሉ እንስሶች ዐይነት
(ዘዳ. 14፥3-21)
1እግዚአብሔር ለሙሴና ለአሮን እንዲህ አላቸው፤ 2“ይህን ለእስራኤል ሕዝብ ንገሩ፤ በምድሪቱ ከሚገኙት እንስሶች መብላት የምትችሉት እነዚህን ነው፦ 3ሰኮናው ስንጥቅ የሆነውንና የሚያመሰኳውን እንስሳ ትበላላችሁ፤ 4ነገር ግን ከሚያመሰኩት ወይም ሰኮናቸው ስንጥቅ ከሆነው የሚከተሉትን አትበሉም፤ ግመል ያመሰኳል፤ ነገር ግን ሰኰናው ስላልተሰነጠቀ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ይሁን። 5ሽኮኮ ያመሰኳል፤ ነገር ግን ሰኰናው ስላልተሰነጠቀ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ይሁን። 6ጥንቸልም ያመሰኳል፤ ንገር ግን ሰኰናው ስላልተሰነጠቀ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ይሁን። 7ዐሳማዎችንም አትብሉ፤ እነርሱ ሰኰናቸው የተሰነጠቀ ቢሆንም ስለማያመሰኩ በእናንተ ዘንድ እንደ ርኩስ የሚቈጠሩ ይሁኑ። 8ለእናንተ የረከሱ ስለ ሆኑ እነዚህን እንስሶች አትብሉ፤ በድናቸውንም እንኳ አትንኩ።
9“በባሕሮችና በወንዞች ውስጥ ካሉት ክንፍና ቅርፊት ያላቸውን ሁሉ ብሉ፤ 10ነገር ግን በውሃ ውስጥ የሚገኘው ክንፍና ቅርፊት የሌለው ፍጥረት ሁሉ መበላት የለበትም። 11እንደነዚህ ያሉት እንስሶች በእናንተ ዘንድ የረከሱ ሆነው መቈጠር አለባቸው፤ እነርሱን መብላት ቀርቶ በድናቸውን መንካት እንኳ የለባችሁም። 12ስለዚህ በውሃ ውስጥ የሚኖሩ ክንፍና ቅርፊት የሌላቸው ፍጥረቶች ሁሉ በእናንተ ዘንድ የተጠሉ ይሁኑ።
13“ከወፎች ወገን ልትጸየፏቸው የሚገባና የማይበሉ እነዚህ ናቸው፤ ንስር፥ ገዲ፥ ዓሣ አውጪ፥ 14ጭላት፥ ጭልፊት በየዐይነቱ 15ቊራ ሁሉ በየወገኑ፥ 16ሰጐን፥ ጠላቋ፥ ዝይ፥ በቋል፥ በየዐይነቱ፥ 17ጒጒት፥ እርኩም፥ ጋጋኖ፥ 18የውሃ ዶሮ፥ ይብራ፥ ጥንብ አንሣ አሞራ፥ 19ሽመላ፥ ሳቢሳ በየዐይነቱ፥ ጅንጁላቴ ወፍ፥ የሌሊት ወፍ።
20“ክንፍ ያላቸው በአራት እግር የሚንቀሳቀሱ ፍጥረቶች ሁሉ የረከሱ ናቸው፤ 21ነገር ግን ከእነርሱ መካከል ከእግሮቻቸው በላይ በምድር ላይ የሚዘሉባቸው ቅልጥሞች ካሉአቸው ተንቀሳቃሾች እነዚህን ትበላላችሁ፤ 22ይኸውም አንበጣዎችን፥ በዐይነታቸው ፌንጣዎችን በየዐይነታቸው፥ ኲብኲባዎችን በየዐይነታቸው 23ነገር ግን ሌሎች ክንፎችና አራት እግሮች ያሉአቸው ፍጥረቶች እንደ ርኩስ ይቈጠሩ።
24“በሚከተሉት እንስሶች ርኩሳን ትሆናላችሁ፤ የእነርሱን በድን የሚነካ እስከ ማታ ርኩስ ይሆናል፤ 25ከእነርሱም በድን የሚያነሣ ልብሱን ይጠብ፤ እስከ ማታም ርኩስ ይሁን፤ 26ሰኰና ያለው፥ ነገር ግን ሰኰናው በሙሉ ያልተሰነጠቀና የማያመሰኩ እንስሳ ሁሉ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ይሆናል፤ እርሱን የሚነካ ሁሉ ይረክሳል፤ 27በአራት እግሮቹ ከሚሄድ እንስሳ በመዳፎቹ ላይ የሚሄድ በእናንተ ዘንድ የረከሰ ይሆናል፤ የእርሱንም በድን የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ርኩስ ይሆናል፤ 28በድናቸውንም የሚያነሣ ልብሱን ይጠብ፤ እስከ ማታም ርኩስ ይሆናል፤ እነርሱም በእናንተ ዘንድ ርኩሳን ናቸው።
29“በምድር ላይ ከሚንቀሳቀሱ ፍጥረቶች እነዚህ በእናንተ ዘንድ ርኩሳን ናቸው፦ ፍልፈል፥ አይጥ፥ እንሽላሊት፥ 30ገበሎ፥ አዞ፥ ኤሊ፥ አርጃኖ፥ እስስት፥ 31ከሚንቀሳቀሱት ሁሉ ርኩሳን የሚሆኑት እነዚህ ናቸው፤ እነርሱንም ሆነ በድናቸውን የሚነካ ሁሉ እስከ ምሽት ድረስ ርኩስ ይሁን። 32በድናቸው የሚወድቅበት ነገር ሁሉ ይረክሳል፤ ይኸውም ከእንጨት የተሠሩ ዕቃዎችን፥ ልብስን፥ ቆዳን ወይም ከረጢት የመሳሰሉትንና ሌላውንም ነገር ሁሉ ይጨምራል፤ የእነርሱ በድን የነካው ይህን የመሰለ ዕቃ ሁሉ በውሃ ውስጥ ተነክሮ ይቈይ፤ እስከ ምሽትም ድረስ ርኩስ ሆኖ ከዚያ በኋላ ንጹሕ ይሆናል። 33ከነርሱ የአንዳቸው በድን በሸክላ ዕቃ ውስጥ ቢወድቅ፥ በዕቃው ውስጥ ያለው ነገር ሁሉ ስለሚረክስ፥ ሸክላውን ስበሩት። 34የሚበላ ምግብ ሁሉ ከሸክላው ዕቃ የውሃ ነጠብጣብ ቢያርፍበት፥ ርኩስ ይሆናል፤ የሚጠጣም ነገር ቢሆን በዚያ ሸክላ ዕቃ ውስጥ ካለ ርኩስ ነው። 35ማንኛውም በድን የሚወድቅበት ነገር ሁሉ ርኩስ ስለ ሆነ፥ ተጸየፉት፤ ክፍት ምድጃም ሆነ ዝግ ምድጃ ይሰበር። 36ሌላው ነገር ሁሉ የእነዚህ እንስሶች በድን ሲነካው የሚረክስ ቢሆንም ምንጭ ወይም የውሃ ጒድጓድ አይረክስም። 37ለዘር በተቀመጠ እህል ላይ ከእነዚህ በድኖች አንዱ ቢያርፍበት ዘሩ ንጹሕ ነው፤ 38ነገር ግን በዘሩ ላይ ውሃ ከፈሰሰበት በኋላ አንዳች በድን ቢነካው ዘሩ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ይሆናል።
39“ከሚበሉትም ቢሆን ማናቸውም እንስሳ ቢሞት የሚነካው ሁሉ እስከ ምሽት ርኩስ ነው። 40ማንም ከዚህ እንስሳ ማንኛውንም ክፍል ቢበላ ልብሱን ይጠብ፤ እስከ ምሽት ድረስ ርኩስ ይሁን፤ ማንም ሰው የዚያን እንስሳ በድን ቢሸከም ልብሱን ይጠብ፤ እርሱም እስከ ምሽት ድረስ ርኩስ ይሁን።
41“በምድር ላይ በደረታቸው እየተሳቡ የሚንቀሳቀሱ ትናንሽ ነፍሳት ሁሉ የማይበሉና በእናንተ ዘንድ የተጠሉ ይሁኑ፤ 42በደረት የሚሳቡ፥ በአራት እግር የሚሄዱ ወይም ብዙ እግር ያሉአቸው ሁሉ የማይበሉና የተጠሉ ይሁኑ። 43ከነዚህ ውስጥ ማንኛውንም በመብላት ራሳችሁን አታርክሱ፤ 44እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፤ እኔ ቅዱስ ስለ ሆንኩ እናንተም ራሳችሁን የተቀደሰ አድርጉ፤ በደረታቸው እየተሳቡ የሚንቀሳቀሱትን ነፍሳት በመብላት ራሳችሁን አታርክሱ። #ዘሌ. 19፥2፤ 1ጴጥ. 1፥16። 45አምላካችሁ እሆን ዘንድ ከግብጽ ምድር መርቼ ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ስለዚህም እኔ ቅዱስ ስለ ሆንኩ እናንተም ቅዱሳን ሁኑ።
46“ይህ እንግዲህ በውሃ ውስጥ ስለሚኖሩና በምድር ላይ ስለሚንቀሳቀሱ ስለ እንስሶችና ወፎች ሁሉ የተሰጠ ሕግ ነው፤ 47ንጹሕ በሆነውና ንጹሕ ባልሆነው መካከል ያለውን ልዩነት ለማወቅ፥ ይኸውም በሚበሉትና በማይበሉት እንስሶች መካከል ያለውን ልዩነት ለመረዳት ብርቱ ጥንቃቄ አድርጉ።”
Currently Selected:
ኦሪት ዘሌዋውያን 11: አማ05
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997