ኦሪት ዘሌዋውያን 10
10
ናዳብና አቢሁ የፈጸሙት በደል
1ናዳብና አቢሁ የተባሉት ሁለቱ የአሮን ልጆች እያንዳንዳቸው ጥናቸውን ወስደው፥ የእሳት ፍም ጭረው ጨመሩበት፤ በእርሱም ላይ ዕጣን አድርገው ወደ እግዚአብሔር አቀረቡ፤ ያን ዐይነት እሳት ያቀርቡ ዘንድ እግዚአብሔር ስላላዘዛቸው፤ ያ እሳቱ የተቀደሰ አልነበረም፤ 2ከዚህም የተነሣ በድንገት ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከ እሳት ስለ በላቸው በእግዚአብሔር ፊት ሞቱ፤ 3ሙሴም አሮንን “እግዚአብሔር ‘በፊቴ ቀርቦ የሚያገለግለኝ ሁሉ ቅድስናዬን ያክብር፤ እኔም በሕዝቤ ፊት የተከበርኩ እሆናለሁ’ እያለ በተናገረበት ጊዜ ይህንኑ ማስጠንቀቁ ነበር” አለው።
አሮንም መልስ ሳይሰጥ ዝም አለ።
4ሙሴም ዑዚኤል የተባለው የአሮን አጐት ልጆች የሆኑትን ሚሻኤልንና ኤልጻፋንን ጠርቶ “ኑ የእነዚህን የወንድሞቻችሁን ሬሳ ከተቀደሰው ድንኳን አንሥታችሁ ከሰፈር ወደ ውጪ አውጡ” አላቸው። 5እነርሱም ልብሰ ተክህኖአቸውን ሳያወልቁ መጥተው ሬሳዎቹን ሙሴ ባዘዛቸው መሠረት ከሰፈር ወደ ውጪ አወጡ።
6ከዚህ በኋላ ሙሴ አሮንን፥ እንዲሁም አልዓዛርና ኢታማር የተባሉትን ሁለቱን የአሮንን ልጆች እንዲህ አላቸው፤ “ለሐዘን ብላችሁ ጠጒራችሁን አትላጩ፤ ልብሳችሁንም አትቅደዱ፤ ይህን ብታደርጉ ግን ትሞታላችሁ፤ እግዚአብሔርም በሕዝቡ ላይ ቊጣውን ያወርዳል፤ ነገር ግን ወንድሞቻችሁ እስራኤላውያን ከእግዚአብሔር በተላከ እሳት ስለሞቱት ልጆች እንዲያለቅሱ ተፈቅዶላቸዋል። 7እግዚአብሔር ባዘዘው የቅባት ዘይት የተቀደሳችሁ ስለ ሆነ ከመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ወደ ውጪ አትውጡ፤ አለበለዚያ ትሞታላችሁ፤” አላቸው፤ እነርሱም ሙሴ እንዳዘዛቸው አደረጉ።
የካህናት መመሪያ ሕግ
8እግዚአብሔር አሮንን እንዲህ አለው፥ 9“አንተና ልጆችህ የወይን ጠጅ ወይም ሌላ የሚያሰክር መጠጥ ጠጥታችሁ ወደ መገናኛው ድንኳን እንዳትገቡ ተጠንቀቁ፤ ይህን ብታደርጉ ትሞታላችሁ፤ ይህም ሕግ ከእናንተ በኋላ በሚነሣውም ትውልድ ዘንድ ሁሉ ተጠብቆ መኖር አለበት። 10እናንተ በተቀደሰውና ባልተቀደሰው፥ በንጹሕና ርኩስ በሆነው መካከል ያለውን ልዩነት ማወቅ አለባችሁ፤ 11በሙሴ አማካይነት እግዚአብሔር የሰጠውን ድንጋጌ ሁሉ ለእስራኤል ሕዝብ አስተምሩ።”
12ሙሴም አሮንንና ከሞት የተረፉትን ሁለቱን ልጆቹን አልዓዛርንና ኢታማርን እንዲህ አላቸው፦ “ለእግዚአብሔር ከቀረበው የምግብ መባ የተረፈውን ወስዳችሁ እርሾ ያልነካው ቂጣ ጋግሩ፤ እርሱም እጅግ የተቀደሰ መባ ስለ ሆነ በመሠዊያው አጠገብ ብሉት። 13ለእግዚአብሔር ከሚቀርበው የምግብ መባ ተከፍሎ ለአንተና ለልጆችህ የተመደበ ድርሻ ስለ ሆነ በተቀደሰ ስፍራ ብሉት። ይህን እንድታደርጉ እግዚአብሔር አዞኛል። #ዘሌ. 6፥14-18። 14ነገር ግን በመወዝወዝ ልዩ መባ ሆኖ ለእግዚአብሔር ከቀረበ በኋላ የካህናቱ ድርሻ እንዲሆን ስለ ተፈቀደ ፍርምባውንና ወርቹን አንተና ቤተሰብህ ሴቶች ልጆችህ ጭምር ትበሉታላችሁ፤ ይህንንም በተቀደሰ ስፍራ ትበሉታላችሁ፤ ይህም የእስራኤል ሕዝብ የአንድነት መሥዋዕት አድርገው ከሚያቀርቡት መባ ሁሉ ተከፍሎ ለአንተና ለልጆችህ ተሰጥቶአል። 15ስቡ ለእግዚአብሔር የምግብ መባ ሆኖ በሚቀርብበት ጊዜ ወርቹንና ፍርምባውን ያመጣሉ፤ ይህም ሁሉ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ለአንተና ለልጆችህ ለዘለዓለም የተመደበ ድርሻ ይሆናል።”
16ሙሴ ስለ ኃጢአት ስርየት መሥዋዕት በመሆን ቀርቦ የነበረውን ፍየል ምን እንዳደረጉት በጠየቀ ጊዜ ተቃጥሎ እንደ ነበር ተረዳ፤ ይህም ነገር በአልዓዛርና በኢታማር ላይ ሙሴን ስላስቈጣው እንዲህ ሲል ጠየቀ፥ 17“ስለ ኃጢአት ስርየት የቀረበውን መባ ስለምን በተቀደሰ ስፍራ አልበላችሁትም፤ እርሱ እጅግ የተቀደሰ ነው፤ እርሱንም የሕዝቡ ኃጢአት ማስወገጃ እንዲሆን እግዚአብሔር ለእናንተ ሰጥቶአችኋል፤ #ዘሌ. 6፥24-26። 18ደሙ ወደተቀደሰው ድንኳን ስላልገባ እኔ ባዘዝኳችሁ መሠረት በዚያው በተቀደሰው ስፍራ የቀረበውን መሥዋዕት መመገብ ነበረባችሁ።”
19አሮንም “ስለ ኃጢአት ስርየት የቀረበውን መሥዋዕት ዛሬ በልቼው ቢሆን ኖሮ ለካ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኝ ኖሮአልን? እነሆ ሕዝቡ ዛሬ ስለ ኃጢአት ስርየት የሚቀርበውን መሥዋዕትና የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አምጥተዋል፤ ነገር ግን እነዚህ እንደዚህ ያሉ ነገሮች በእኔ ላይ ደረሱ” ሲል መለሰ፤ 20ሙሴም ይህን በሰማ ጊዜ በተሰጠው መልስ ተደሰተ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘሌዋውያን 10: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997