የይሁዳ መልእክት 1
1
1የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይና የያዕቆብ ወንድም ከሆነው ከይሁዳ፥
ለተጠራችሁት፥ በእግዚአብሔር አብ ለተወደዳችሁት፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ለተጠበቃችሁት ሁሉ፥ #ማቴ. 13፥55፤ ማር. 6፥3።
2ምሕረት፥ ሰላምና ፍቅርም ይብዛላችሁ።
ሐሰተኞች መምህራን
3ወዳጆች ሆይ! ስለ ጋራ መዳናችን ልጽፍላችሁ በብርቱ ፈልጌ ነበር፤ አሁን ግን በማያዳግም ሁኔታ እግዚአብሔር ለሕዝቡ አንድ ጊዜ ስለ ሰጠው እምነት በብርቱ እንድትጋደሉ ለመምከር ልጽፍላችሁ ግድ ሆነብኝ። 4የሚፈረድባቸው መሆኑ ከብዙ ጊዜ በፊት የተጻፈባቸው አንዳንድ ሰዎች ወደ እናንተ ሾልከው ገብተዋል፤ እነርሱ የአምላካችንን ጸጋ በስድነት የሚለውጡ እግዚአብሔርን የማያመልኩ ናቸው፤ እርሱ ብቻ ገዢአችንና ጌታችን የሆነን ኢየሱስ ክርስቶስንም ይክዳሉ።
5ይህን ሁሉ አስቀድማችሁ አንድ ጊዜ የምታውቁት ቢሆንም እንኳ ጌታ ሕዝቡን ከግብጽ አገር አውጥቶ እንዳዳነና ያላመኑትንም በኋላ እንዳጠፋቸው ላስታውሳችሁ እወዳለሁ። #ዘፀ. 12፥51፤ ዘኍ. 14፥29-30። 6እንዲሁም ማዕርጋቸውን ባለመጠበቅ ስፍራቸውን የተዉትን መላእክት አስታውሱ፤ እነርሱን እግዚአብሔር እስከ ታላቁ የፍርድ ቀን ድረስ በዘለዓለም እስራት፥ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ጠብቆ አቆይቷቸዋል። 7በዚሁ ዐይነት ሰዶምና ገሞራ በዙሪያቸው ያሉ ከተሞችም ሴሰኞች ሆኑ፤ ከተፈጥሮ ሥርዓት ውጪም ዝሙት ፈጸሙ። ስለዚህ እነርሱ በዘለዓለም እሳት ለሚቀጡት ምሳሌ ሆነዋል። #ዘፍ. 19፥1-24።
8እንዲሁም እነዚህ ሰዎች በሕልማቸው እየተመሩ ሥጋቸውን ያረክሳሉ፤ ለባለ ሥልጣኖችም አይታዘዙም፤ በሰማይ ክብር ያላቸውንም ይሳደባሉ። 9የመላእክት አለቃ ሚካኤል እንኳ ስለ ሙሴ አስከሬን ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ “ጌታ ይገሥጽህ” አለው እንጂ የስድብ ቃል አልተናገረም። #ዳን. 10፥13፤21፤ 12፥1፤ ራዕ. 12፥7፤ ዘዳ. 34፥6፤ ዘካ. 3፥2። 10እነዚህ ሰዎች ግን ለማስተዋል ያቃታቸውን ነገር ሁሉ ይሳደባሉ፤ አእምሮ እንደሌላቸው እንስሶች በተፈጥሮ ስሜት የሚያውቁት ነገር ቢኖር እንኳ በእርሱ ይጠፋሉ። 11በቃየል መንገድ ስለ ሄዱ፥ ለገንዘብ ብለው በበለዓም ስሕተት ስለ ወደቁ፥ ቆሬም እንደ ተቃወመ በመቃወማቸው ስለ ጠፉ ወዮላቸው! #ዘፍ. 4፥3-8፤ ዘኍ. 22፥1-35፤ 16፥1-35። 12እነዚህ ሰዎች ያለ ኀፍረት በመዳራት በአንድነት ግብዣችሁ ላይ ሲገኙ እንቅፋት ይሆኑባችኋል፤ እነርሱ የሚያስቡት ስለ ራሳቸው ብቻ ነው፤ በነፋስ እንደሚገፋ፥ ዝናብ እንደሌለው ደመና ናቸው። በፍሬ ወራት እንኳ ፍሬ እንደማይገኝበት፥ ከስሩ እንደ ተነቀለና ሁለት ጊዜ እንደ ሞተ ዛፍ ናቸው። 13የአሳፋሪ ድርጊታቸውን ዐረፋ የሚደፍቁ፥ እንደ ተቈጣ የባሕር ማዕበል ናቸው፤ ድቅድቅ ጨለማ ለዘለዓለም እንደሚጠብቃቸውና፥ እንደሚንከራተቱ ኮከቦች ናቸው።
14ከአዳም ጀምሮ ሰባተኛ ትውልድ የሆነው ሔኖክ ሲናገር እንዲህ ብሎአል፦ “እነሆ እግዚአብሔር እልፍ አእላፋት ቅዱሳን መላእክቱ ጋር ሆኖ በሁሉም ላይ ለመፍረድ ይመጣል፤ #ዘፍ. 5፥18፤21-24። 15እነዚያን እግዚአብሔርን የማያመልኩትን ሰዎች ባደረጉአቸው ክፉ ነገሮች ምክንያት ይቀጣቸዋል፤ እግዚአብሔርም በእውነቱ በእነዚህ እርሱን በማያመልኩ ኃጢአተኞች ላይ በእርሱ ላይ ስለ ተናገሩአቸው ክፉ ነገሮች ሁሉ ይፈርድባቸዋል።”
16እነዚህ ሰዎች ሁልጊዜ የሚያጒረመርሙና በምንም ነገር የማይደሰቱ ናቸው፤ የራሳቸውን ክፉ ምኞት የሚከተሉ ናቸው፤ አፋቸው በትዕቢት ቃል የተሞላ ነው፤ የራሳቸውን ጥቅም በመፈለግ ሰውን ይለማመጣሉ።
ማስጠንቀቂያና ምክር
17እናንተ ግን ወዳጆች ሆይ! የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት ከዚህ በፊት የተናገሩትን ቃል አስታውሱ። 18እነርሱ “በመጨረሻው ዘመን ከእግዚአብሔር ፈቃድ የራቁ የገዛ ራሳቸውን ክፉ ምኞት የሚከተሉ ፌዘኞች ይመጣሉ” ብለዋችሁ ነበር። #2ጴጥ. 3፥3። 19እነርሱ ሰውን የሚለያዩ፥ የሥጋን ምኞት የሚከተሉ፥ መንፈስ ቅዱስ የሌላቸው ሰዎች ናቸው። 20እናንተ ግን ወዳጆች ሆይ፥ ከሁሉ በላይ በተቀደሰው እምነታችሁ ራሳችሁን ለማነጽ ትጉ፤ በመንፈስ ቅዱስም ኀይል ጸልዩ። 21ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በምሕረቱ ወደ ዘለዓለም ሕይወት እንዲያደርሳችሁ በመጠባበቅ ራሳችሁን በእግዚአብሔር ፍቅር ውስጥ ጠብቁት።
22ለሚጠራጠሩ ሰዎች ርኅራኄ አድርጉላቸው፤ 23አንዳንዶችን ከእሳት አውጥታችሁ አድኑአቸው፤ ለሌሎች በፍርሃት ራሩላቸው፤ ሆኖም በኃጢአት የረከሰውን ሰውነታቸውን የነካውን ልብስ እንኳ ሳይቀር ጥሉ።
የምስጋና ጸሎት
24እንዳትወድቁ ሊያደርጋችሁና ነቀፋ የሌለባችሁ አድርጎ በደስታ በክብሩ ፊት ሊያቀርባችሁ ለሚችል፥ 25እርሱ ብቻ መድኃኒታችን ለሆነው አምላክ፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ከጥንት ጀምሮ፥ አሁንም፥ ለዘለዓለምም ክብርና ግርማ፥ ኀይልና ሥልጣንም ይሁን! አሜን።
Currently Selected:
የይሁዳ መልእክት 1: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997