የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ኢያሱ 7

7
ዓካን የፈጸመው በደል
1እስራኤላውያን ግን የተከለከሉ ነገሮችን በተመለከተ ታማኞች ሆነው አልተገኙም፤ ከይሁዳ ነገድ የሆነው ዓካን፥ የከርሚ ልጅ፥ የዘብዲ የልጅ ልጅ፥ የዛራ ልጅ ከተከለከሉት ነገሮች በመውሰድ በእስራኤል ላይ የእግዚአብሔርን ቊጣ አስነሣ።
2ኢያሱ በኢያሪኮ ሳለ በቤትአዌን አጠገብ ከቤትኤል በስተምሥራቅ የምትገኘውን “ዐይ” ተብላ የምትጠራውን ከተማና የምድሪቱን አቀማመጥ አጥንተው ይመለሱ ዘንድ ጥቂት ሰዎችን ላከ። ይህንንም በትእዛዙ መሠረት ከፈጸሙ በኋላ፥ 3ለኢያሱ ከዚህ የሚከተለውን ማስረጃ አቀረቡለት፦ “እነርሱ ጥቂቶች ስለ ሆኑ በዐይ ላይ አደጋ ለመጣል ያለውን ሰው ሁሉ በአጠቃላይ ማዝመት አያስፈልግም፤ ሁለት ወይም ሦስት ሺህ ሰዎች ብቻ ላክ፤ በዚያ ለመዋጋት መላውን ሠራዊት አትላክ።” 4ስለዚህም ሦስት ሺህ እስራኤላውያን ዘምተው አደጋ ጣሉባት፤ ነገር ግን እነርሱ ከዐይ ወታደሮች ፊት ሸሹ፤ 5የዐይ ሰዎችም ወደ ሠላሳ ስድስት ያኽል ሰዎችን ገደሉባቸው፤ ከከተማይቱ ቅጥር በር ጀምሮ እስከ ሼባሪዎ ቊልቊለት ድረስ እየገደሉ አባረሩአቸው፤ የሕዝቡም ልብ ቀልጦ እንደ ውሃ ፈሰሰ። 6ኢያሱና የእስራኤል መሪዎች በሐዘን ልብሳቸውን ቀደዱ፤ በእግዚአብሔርም ታቦት ፊት እስከ ማታ ድረስ በግንባራቸው ተደፉ፤ ሐዘናቸውን ለመግለጥ በራሳቸው ላይ ትቢያ ነሰነሱ። 7ኢያሱም እንዲህ ሲል ጸለየ፦ “ወዮ! እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! ይህን ሕዝብ ለምን ዮርዳኖስን አሻገርከው? አሞራውያን እንዲያጠፉን ለእነርሱ አሳልፈህ ለመስጠት ነውን? ከዮርዳኖስ ማዶ ብንቀመጥ እንዴት በተሻለን ነበር! 8አምላክ ሆይ፥ እስራኤል ከጠላቶቹ ፊት ከሸሸ እንግዲህ ምን እላለሁ? 9ከነዓናውያንና ሌሎችም በዚህች ምድር የሚኖሩት ሁሉ ይህን ነገር ይሰማሉ፤ ስለዚህም ዙሪያችንን ከበው ሁላችንንም ይፈጁናል፤ ታዲያ ስለ ክብርህ የምታደርገው ምንድን ነው?”
10እግዚአብሔር ኢያሱን እንዲህ አለው፤ “ተነሥ! ስለምን በግንባርህ ወደቅኽ? 11እስራኤላውያን በድለዋል፤ እንዲጠብቁት ያዘዝኳቸውንም ቃል ኪዳን አፍርሰዋል፤ ከተከለከሉት ነገሮች ወስደዋል፤ ሰርቀዋል፤ ከራሳቸው ንብረት ጋር በማቀላቀል አታላዮች ሆነዋል። 12እስራኤላውያን ጠላቶቻቸውን መቋቋም ያልቻሉበትም ምክንያት ይኸው ነው፤ እነርሱ ራሳቸው እንዲጠፉ ስለ ተፈረደባቸው ከጠላቶች ፊት ወደ ኋላ ይሸሻሉ። እንዲደመሰስ የታዘዘውን ነገር ከመካከላችሁ ካላጠፋችሁ እኔ ከእናንተ ጋር አልሆንም። 13ሂድ! ሕዝቡን አንጻ! ‘በመካከላችሁ የተከለከለ ነገር ስላለ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ለነገ ራሳችሁን አንጹ!’ ይላል በላቸው። እስራኤል ሆይ! ይህን የተከለከለ ነገር ከመካከልህ ካላስወገድህ በጠላቶችህ ፊት ልትቆም አትችልም። 14ስለዚህ ነገ ጧት በየነገዳችሁ ቅረቡ፤ እግዚአብሔር የሚለየው ነገድ በየጐሣው ይቅረብ፤ እግዚአብሔር የሚለየው ጐሣ በየቤተሰቡ ይቅረብ፤ እግዚአብሔር የሚለየው ቤተሰብ በየግለሰቡ ይቅረብ፤ 15እርም የሆኑ (የተከለከሉ) ነገሮች የተገኙበትም ሰው የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ስላፈረሰና በእስራኤል ላይ በደል ስለ ፈጸመ እርሱና የእርሱ የሆነ ሁሉ በእሳት ይቃጠል።”
16በማግስቱም ማለዳ ኢያሱ እስራኤላውያንን በየነገዳቸው አምጥቶ አቀረባቸው፤ ከዚያም የይሁዳ ነገድ ለብቻው ተለየ፤ 17ኢያሱም የይሁዳን ነገድ በየጐሣው አቀረበ፤ ከዚያም በኋላ የዛራሕ ጐሳ ለብቻው ተለየ፤ የዛራሕንም ጐሣ በየቤተሰቡ አቀረበው፤ የዛብዲም ቤተሰብ ለብቻው ተለየ፤ 18የዛብዲንም ቤተሰብ በየግለሰቡ ለይቶ አቀረበ፤ በመጨረሻም የዛብዲ የልጅ ልጅ የሆነው የካርሚ ልጅ ዓካን ለብቻው ተለየ፤ 19ኢያሱም ዓካንን “ልጄ ሆይ፥ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን አክብር፤ ለእርሱም ተናዘዝ ያደረግኸውንም ከእኔ ሳትደብቅ ንገረኝ” አለው።
20ዓካንም እንዲህ ሲል መለሰ፥ “እውነት ነው፤ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን የበደልኩ እኔ ነኝ፤ እነሆ፥ ያደረግኹትም ከዚህ የሚከተለው ነው፤ 21ካገኘነው ዕቃ መካከል ውብ የሆነ የባቢሎናውያን ካባ፥ ሁለት ኪሎ ያኽል የሚመዝን ብርና ግማሽ ኪሎ ያህል የሚመዝን ምዝምዝ ወርቅ አየሁ፤ እነርሱንም ለማግኘት ብርቱ ፍላጎት ስላደረብኝ ወስጃቸዋለሁ፤ እነርሱንም ብሩ ከታች ሆኖ በድንኳኔ ውስጥ በመሬት ተቀብረዋል።”
22ከዚህ በኋላ ኢያሱ መልእክተኞችን ላከ፤ እነርሱም ወደ ድንኳኑ እየሮጡ ሄዱ፥ እዚያም ብር ከስር ሆኖ የተቀበሩት እርም የሆኑ ዕቃዎች ነበሩ፤ 23እነርሱንም ከድንኳኑ በማውጣት፥ ወደ ኢያሱና ወደ እስራኤላውያን አምጥተው በእግዚአብሔር ፊት አኖሩአቸው። 24ኢያሱም ከመላው የእስራኤል ሕዝብ ጋር ዓካንን ይዞ ብሩን፥ ካባውን፥ የወርቅ ምዝምዙን ከዓካን ወንዶችና ሴቶች ልጆች ጋር ከብቶቹን፥ አህዮቹንና በጎቹን ጭምር፥ ድንኳኑንና የእርሱ ንብረት የሆነውን ሁሉ ሰብስቦ፥ ወደ አኮር ሸለቆ አመጣቸው፤ 25ኢያሱም “ይህን ሁሉ መከራ በእኛ ላይ ያመጣህብን ስለምንድን ነው? እነሆ! በአንተም ላይ ዛሬ እግዚአብሔር መከራን ያመጣብሃል!” አለው። ከዚህ በኋላ ሕዝቡ ሁሉ ዓካንን በድንጋይ ወግረው ገደሉት፤ ቤተሰቡንም በድንጋይ ወግረው ንብረቱን ሁሉ አቃጠሉ፤ 26በእርሱም ላይ እስከ ዛሬ ድረስ የሚታይ ታላቅ የድንጋይ ክምር ከመሩበት፤ እግዚአብሔርም ከቊጣው ተመለሰ፤ ስለዚህም ያ ቦታ የአኮር ሸለቆ ተብሎ ይጠራል። #7፥26 የአኮር ሸለቆ፦ በዕብራይስጡ የችግር ሸለቆ ማለት ነው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ