የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ኢያሱ 5

5
1ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተምዕራብ ያሉ የአሞራውያን ነገሥታትና በሜዲትራኒያን ባሕር ዳርቻ ጠረፉን ተከትለው የሚኖሩ የከነዓናውያን ነገሥታት ሁሉ የእስራኤል ሕዝብ እስኪሻገሩ ድረስ እግዚአብሔር የዮርዳኖስን ወንዝ ውሃ እንዳደረቀላቸው በሰሙ ጊዜ፤ በፍርሃት ልባቸው ቀለጠ፤ ከዚያም በኋላ እስራኤላውያንን ለመቋቋም ድፍረት አጡ።
በጌልገላ የተደረገ ግዝረት
2በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር ኢያሱን “ከባልጩት የተሠራ መቊረጫ አዘጋጅተህ እስራኤላውያንን እንደገና ግረዛቸው” አለው። 3ኢያሱም እግዚአብሔር እንዳዘዘው በማድረግ “የግዝረት ኮረብታ” ተብሎ በሚጠራው ስፍራ እስራኤላውያንን ገረዘ። 4ኢያሱ እነርሱን የገረዘበት ምክንያት ከግብጽ ምድር የወጡት ለወታደርነት ብቃት የነበራቸው ወንዶች ሁሉ በበረሓው ጒዞ ጊዜ ሞተው ስለ ነበረ ነው። 5በመጀመሪያ ከግብጽ ምድር የወጡት ወንዶች ሁሉ ተገርዘው የነበሩ ቢሆኑም እንኳ በበረሓው ጒዞ ጊዜ የተወለዱት ወንዶች አልተገረዙም ነበር። 6ከግብጽ ምድር የወጡት ለወታደርነት ብቃት የነበራቸው ወንዶች የእግዚአብሔርን ቃል ባለመስማታቸው ሁሉም እስኪያልቁ ድረስ እስራኤላውያን በበረሓ ለአርባ ዓመት ተጓዙ። ለልጅ ልጆቻቸው ሊሰጥ ለቀድሞ አባቶቻቸው ቃል ገብቶ የነበረውን በማርና በወተት የበለጸገውን ምድር በምድረ በዳ ያለቁት ልጆቻቸው እንደማያዩት አረጋግጦ ነበር። #ዘኍ. 14፥28-35። 7ኢያሱ የገረዛቸው እግዚአብሔር በእነርሱ ቦታ ያስነሣቸውን ልጆቻቸውን ነው፤ እነርሱ በጉዞ ላይ በነበሩ ጊዜ ስላልተገረዙ ሸለፈታሞች ነበሩ።
8ሰዎች ሁሉ ከተገረዙ በኋላ ቊስላቸው እስኪድን ድረስ በሰፈር ቈዩ። 9እግዚአብሔር ኢያሱን፦ “እነሆ፥ ዛሬ እኔ ከእናንተ ላይ የግብጽን ነውር አስወግጄላችኋለሁ” አለው። ያም ቦታ እስከ ዛሬ ድረስ ጌልጌላ ተብሎ ይጠራል። #5፥9 “ነውር” ያለው በግብጽ ምድር በባርነት መኖራቸውን ነው። #5፥9 ጌልጌላ፦ በዕብራይስጥ “አንከባለለ ወይም አስወገደ” ማለት ነው።
10እስራኤላውያን ከኢያሪኮ አጠገብ ባለው ሜዳ በጌልገላ ሰፍረው ሳሉ፥ ከወሩ በዐሥራ አራተኛው ቀን ምሽት የፋሲካን በዓል አከበሩ፤ #ዘፀ. 12፥1-13። 11በከነዓን የበቀለውን እህል መብላት የጀመሩትም በዚያን ቀን ማግስት ነበር፤ የተመገቡትም የተጠበሰ እሸትና ያለ እርሾ የተጋገረ ቂጣ ነበር። 12ከምድሪቱ የሚገኘውን ምግብ መብላት ከጀመሩበት ቀን አንሥቶ መና መዝነቡን አቋረጠ፤ እስራኤላውያንም ከዚያን በኋላ ያን መና ማግኘት አልቻሉም፤ ከዚያን ጊዜ አንሥቶ በከነዓን የበቀለውን እህል መብላት ጀመሩ። #ዘፀ. 16፥35።
ኢያሱና ሰይፍ የያዘው ጐልማሳ
13ኢያሱ በኢያሪኮ አጠገብ ሳለ ሰይፍ የያዘ አንድ ጐልማሳ በድንገት በፊቱ ቆሞ ታየው፤ ኢያሱም ወደ እርሱ ቀረብ ብሎ “አንተ የእኛ ወገን ነህ ወይስ የጠላቶቻችን?” አለው።
14ጐልማሳውም “የእናንተም ሆነ የጠላት ወገን አይደለሁም፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ሠራዊት አዛዥ እንደ መሆኔ መጠን እነሆ፥ መጥቻለሁ” አለ።
ኢያሱም ወደ መሬት ወድቆ ሰገደለትና “ጌታዬ ሆይ፥ እኔ አገልጋይህ ምን ልታዘዝ?” አለው።
15የእግዚአብሔር ሠራዊት አዛዥም “የቆምክባት ምድር የተቀደሰች ስለ ሆነች ጫማህን አውልቅ” አለው፤ ኢያሱም እርሱ እንዳዘዘው አደረገ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ