መጽሐፈ ኢያሱ 4
4
የመታሰቢያ ድንጋዮች ስለ ማቆም የተሰጠ ትእዛዝ
1የእስራኤል ሕዝብ በሙሉ ዮርዳኖስን ከተሻገሩ በኋላ እግዚአብሔር ኢያሱን እንዲህ አለው፦ 2“ከእያንዳንዱ ነገድ አንዳንድ ሰው በመውሰድ ዐሥራ ሁለት ሰዎችን ምረጥ፤ 3በዮርዳኖስ ወንዝ መካከል፥ ካህናቱ ከቆሙበት ከዚያው ስፍራ ዐሥራ ሁለት ድንጋዮች ይዘው እንዲወጡ እዘዛቸው፤ ድንጋዮቹንም ወስደው ዛሬ ማታ በምትሰፍሩበት ስፍራ ያቆሙአቸው ዘንድ ንገር።”
4ኢያሱም የመረጣቸውን ዐሥራ ሁለት ሰዎች ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ 5“በአምላካችሁ በእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት ፊት ቀድማችሁ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ውረዱ፤ በእያንዳንዱ የእስራኤል ነገድ ስም፥ እያንዳንዳችሁ አንዳንድ ድንጋይ በማንሣት በትከሻችሁ ተሸከሙ። 6እነዚህም ድንጋዮች እግዚአብሔር ያደረገውን ነገር ሁሉ ለእስራኤል ሕዝብ የሚያስታውሱ መታሰቢያዎች ይሆናሉ፤ በሚመጡትም ዘመናት ልጆቻችሁ ‘እነዚህ ድንጋዮች ምንድናቸው?’ ብለው በሚጠይቁአችሁ ጊዜ፥ 7እናንተም እንዲህ ብላችሁ ትነግሩአቸዋላችሁ፦ ‘የአምላካችሁ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦት በሚሻገርበት ጊዜ፥ የዮርዳኖስ ወንዝ ውሃ መውረዱን አቆመ፤ ስለዚህም እነዚህ ድንጋዮች በዚህ ስፍራ የተደረገውን ሁሉ ለዘለቄታው ለእስራኤል ሕዝብ የሚያስታውሱ መታሰቢያዎች ናቸው።’ ”
8ሰዎቹም ኢያሱ እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ እግዚአብሔር ለኢያሱ በነገረው መሠረት በእስራኤል ነገዶች ቊጥር ከዮርዳኖስ ወንዝ መካከል ዐሥራ ሁለቱን ድንጋዮች ወደ ሰፈሩበት ቦታ ወስደው አስቀመጡ፤ 9ኢያሱም ደግሞ ካህናቱ የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸክመው በቆሙበት በዮርዳኖስ ወንዝ መካከል ዐሥራ ሁለት የመታሰቢያ ድንጋዮችን አቆሙ፤ እነዚያም ድንጋዮች እስከ ዛሬ በዚያው ይገኛሉ፤ 10ለሕዝቡ እንዲነግር እግዚአብሔር ኢያሱን ባዘዘው መሠረት ሁሉ ነገር እስኪፈጸም ድረስ ካህናቱ በዮርዳኖስ ወንዝ መካከል እንደ ቆሙ ቈዩ፤ ሙሴም ኢያሱን ያዘዘው ይህንኑ ነበር፤ ሕዝቡም ፈጥኖ ወንዙን ተሻገሩ። 11ሁሉም ተሻግረው ካበቁ በኋላ፥ የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙት ካህናት እንደገና ወደ ፊት ቀድመው ሕዝቡን መምራት ጀመሩ። 12ከሮቤልና ከጋድ እንዲሁም ከምናሴ ነገድ እኩሌታ ለጦርነት የተዘጋጁት ሰዎች ሙሴ ባዘዛቸው መሠረት ከሕዝቡ ግንባር ቀደም ሆነው ተሻገሩ። 13ከእነርሱም የተውጣጡ ብዛታቸው አርባ ሺህ ያኽል የሆነ ጦረኞች በእግዚአብሔር ፊት ተሰልፈው በኢያሪኮ አቅራቢያ ወደሚገኘው ሜዳ ተሻገሩ። 14በዚያን ቀን እግዚአብሔር ኢያሱን በእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ፊት ከፍ ከፍ አደረገው፤ ሙሴን ያከብሩት እንደ ነበር ኢያሱንም በሕይወቱ ዘመን ሁሉ አከበሩት።
15ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ኢያሱን እንዲህ አለው፦ 16“የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙት ካህናት ከዮርዳኖስ ወንዝ እንዲወጡ እዘዝ፤” 17ኢያሱም ካህናቱን ከዮርዳኖስ ወንዝ እንዲወጡ አዘዘ። 18የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት የተሸከሙት ካህናት ከዮርዳኖስ ወንዝ መካከል ወጥተው እግሮቻቸው ደረቁን መሬት በረገጡ ጊዜ የዮርዳኖስ ወንዝ ውሃ ወደ ቦታው ተመልሶ እንደ ቀድሞው ሞልቶ ይፈስ ጀመር።
19ሕዝቡ የመጀመሪያው ወር በገባ በዐሥረኛው ቀን፥ የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግረው ከኢያሪኮ በስተምሥራቅ በኩል በሚገኘው በጌልገላ ሰፈሩ። 20በጌልገላም ኢያሱ ከዮርዳኖስ ወንዝ የተወሰዱትን ዐሥራ ሁለት ድንጋዮች አቁሞ፥ 21ለእስራኤል ሕዝብ እንዲህ አለ፦ “በሚመጡት ዘመናት የልጅ ልጆቻችሁ፦ ‘እነዚህ ድንጋዮች ምንድን ናቸው?’ ብለው ወላጆቻቸውን በሚጠይቁአቸው ጊዜ፦ 22የእስራኤል ሕዝብ የዮርዳኖስን ወንዝ በደረቅ ምድር የተሻገሩበት ጊዜ መኖሩን ትነግሩአቸዋላችሁ፤ 23አምላካችን እግዚአብሔር እስክንሻገር ድረስ አስቀድሞ ለእኛ የቀይ ባሕርን እንዳደረቀልን፥ ለእናንተም የዮርዳኖስን ወንዝ እስክትሻገሩ ድረስ ውሃ አድርቆ ያሻገራችሁ መሆኑን ንገሩአቸው፤ 24በዚህም ምክንያት በምድር ላይ የሚኖር ሕዝብ ሁሉ የእግዚአብሔር ኀይል ምን ያኽል ታላቅ እንደ ሆነ ይገነዘባል፤ እናንተም አምላካችሁ እግዚአብሔርን ለዘለዓለም ታከብራላችሁ።”
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢያሱ 4: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997