የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ኢያሱ 3

3
የእስራኤል ሕዝብ የዮርዳኖስን ወንዝ መሻገሩ
1በማግስቱ ኢያሱና የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ማልደው ተነሡ፤ የሺጢምን ሰፈር ለቀው ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ሄዱ፤ ከመሻገራቸውም በፊት በዚያ ሰፈሩ፤ 2ከሦስት ቀን በኋላ የሕዝቡ መሪዎች ወደ ሰፈር ገብተው፥ 3የሚከተለውን ትእዛዝ ሰጡ፦ “የሌዊ ዘር የሆኑት ካህናት የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት ተሸክመው ሲነሡ በምታዩበት ጊዜ፥ ሰፈሩን ለቃችሁ እነርሱን ተከተሉ። 4ከዚህ በፊት ይህን ቦታ ስለማታውቁት የምትሄዱበትን መንገድ እነርሱ ያሳዩአችኋል፤ ነገር ግን ወደ ቃል ኪዳኑ ታቦት አትቅረቡ፤ በእናንተና በቃል ኪዳኑ ታቦት መካከል የሚኖረው ርቀት አንድ ኪሎ ሜትር ያኽል ይሁን።”
5ኢያሱም ሕዝቡን፦ “እግዚአብሔር ነገ በመካከላችሁ ተአምራትን ስለሚያደርግ ራሳችሁን አንጹ” አላቸው። 6የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸክመው ከሕዝቡ በመቅደም እፊት እፊት እንዲሄዱ ለካህናቱ ነገራቸው፤ እነርሱም እንደ ታዘዙት አደረጉ።
7እግዚአብሔርም ኢያሱን እንዲህ አለው፦ “ከሙሴ ጋር እንደ ነበርኩ ከአንተም ጋር የምሆን መሆኔን ያውቁ ዘንድ እኔ ዛሬ በእስራኤላውያን ሁሉ ፊት አንተን ከፍ፥ ከፍ ማድረግ እጀምራለሁ። 8የቃል ኪዳኑን ታቦት ለሚሸከሙት ካህናት፦ ‘ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ በምትደርሱበት ጊዜ በወንዙ ውስጥ ቀጥ ብላችሁ ቁሙ’ ብለህ ንገራቸው።”
9ከዚህ በኋላ ኢያሱ እስራኤላውያንን፦ “ወደዚህ ቅረቡና የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል አድምጡ” አላቸው። 10ኢያሱም ንግግሩን በመቀጠል፦ “ሕያው እግዚአብሔር በመካከላችሁ መሆኑን የምታውቁት እናንተ ወደ ፊት እየገፋችሁ በሄዳችሁ መጠን እርሱ ከነዓናውያንን፥ ሒታውያንን፥ ሒዋውያንን፥ ፈሪዛውያንን፥ ጌርጌሳውያንን፥ አሞራውያንንና ኢያቡሳውያንን ከፊታችሁ የሚያስወጣ በመሆኑ ነው። 11የምድር ሁሉ ጌታ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት በፊታችሁ ቀድሞ ወደ ዮርዳኖስ ማዶ ይሸጋገራል። 12እነሆ፥ ከእያንዳንዱ የእስራኤል ነገድ አንዳንድ ተወካይ በማቅረብ አሁኑኑ ዐሥራ ሁለት ሰዎችን ምረጡ፤ 13የምድርን ሁሉ ጌታ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት የተሸከሙ ካህናት እግሮች ውሃውን በሚነኩበት ጊዜ የዮርዳኖስ ወንዝ ውሃ መውረዱን ያቆማል፤ ከላይ እየጐረፈ የሚመጣውም ውሃ በአንድ ቦታ ተሰብስቦ ይቈለላል።”
14ሕዝቡ ዮርዳኖስን ለመሻገር ድንኳኑን በነቀሉ ጊዜ የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙት ካህናት በሕዝቡ ፊት ይሄዱ ነበር። 15የዮርዳኖስ ወንዝ በመከር ጊዜ ጐርፍ ያለው ቢሆንም የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙት ካህናት ደርሰው እግሮቻቸው የውሃውን ዳር እንደ ነኩ፥ 16ውሃው መውረዱን አቆመ፤ በጻርታን አጠገብ አዳም ተብላ እስከምትጠራው ከተማ ድረስ ተከመረ፤ ወደ ሙት ባሕር ይፈስ የነበረውም ጐርፍ በፍጹም ተቋረጠ፤ ስለዚህም ሕዝቡ ወደ ማዶ ወደ ኢያሪኮ ተሻገሩ። 17ሕዝቡ በደረቅ ምድር እየተራመዱ በሚሻገሩበት ጊዜ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት የተሸከሙ ካህናት ሕዝቡ ሁሉ ተሻግረው እስካበቁ ድረስ በዮርዳኖስ ወንዝ መካከል በደረቅ ምድር ላይ ቆመው ነበር።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ