መጽሐፈ ኢያሱ 2:1-16

መጽሐፈ ኢያሱ 2:1-16 አማ05

ከዚህ በኋላ የነዌ ልጅ ኢያሱ ከሺጢም ሰፈር ሁለት ሰላዮችን ላከ፤ እነርሱም የከነዓንን ምድር በተለይም የኢያሪኮን ከተማ በምሥጢር ሰልለው እንዲመለሱ አዘዛቸው፤ ወደ ከተማይቱ በመጡ ጊዜ “ረዓብ” ተብላ ወደምትጠራ ወደ አንዲት ሴትኛ ዐዳሪ ቤት ገብተው ዐደሩ። “አገሪቱን ለመሰለል ከእስራኤላውያን መካከል ዛሬ ማታ ወደዚህ መጥተዋል” ተብሎ ለኢያሪኮ ንጉሥ ተነገረው። ከዚህ በኋላ የኢያሪኮ ንጉሥ “ምድሪቱን ሊሰልሉ የመጡ ስለ ሆኑ ወደ ቤትሽ የገቡትን ሰዎች አውጥተሽ አስረክቢ!” ብሎ ወደ ረዓብ ትእዛዝ ላከ። ሴቲቱም ሁለቱን ሰዎች ወስዳ ሸሸገቻቸው፤ እርስዋም፦ “አዎን፥ ሰዎቹ ወደ እኔ መጡ፤ ከወዴት እንደ ሆኑ ግን አላውቅም፤ ጊዜው መሽቶ በመጨለሙ በሩ ሲዘጋ ሰዎቹ ወጥተው ሄዱ፤ ወዴት እንደ ሄዱ ግን አላውቅም፤ ፈጥናችሁ ብታሳድዱአቸው ትደርሱባቸዋላችሁ” አለች። እርስዋ ግን ወደ ሰገነቱ አውጥታ በዚያ በረበረበችው በተልባ እግር ውስጥ ሸሽጋቸው ነበር። የንጉሡም መልእክተኞች ከከተማይቱ ወጥተው ሄዱ፤ የቅጽር በሩም ተዘጋ፤ መልእክተኞቹም ሰላዮችን በመፈለግ የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግሮ እስከሚያልፈው ስፍራ ድረስ ሄዱ። ረዓብም ከመተኛታቸው በፊት ወዳሉበት የቤት ጣራ ወጥታ፥ እንዲህ አለቻቸው፦ “የሀገሪቱ ኗሪዎች በሙሉ በፍርሃት ተውጠው ልባቸው ቀለጠ፤ በሁላችንም ላይ ፍርሀት ስላደረብን እግዚአብሔር ምድሪቱን ለእናንተ እንደ ሰጠ ዐውቃለሁ፤ ግብጽን ለቃችሁ በወጣችሁ ጊዜ፥ እግዚአብሔር ቀይ ባሕርን በፊታችሁ እንዴት እንዳደረቀ ሰምተናል፤ ከዮርዳኖስ ወንዝ ማዶ የነበሩትን ሁለቱን የአሞራውያን ነገሥታት ሲሖንንና ዖግን እንዴት እንደ ገደላችሁም ሰምተናል። ስለዚህም ይህን ሁሉ ነገር በሰማን ጊዜ በፍርሃት ልባችን ቀለጠ፤ ወኔአችን ሁሉ ጠፋ፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር በእርግጥ የሰማይና የምድር አምላክ ነው። አሁንም እኔ ለእናንተ መልካም ነገር እንዳደረግሁላችሁ ሁሉ ቤተሰቤን ከጥፋት በማትረፍ መልካም ነገር ታደርጉልኝ ዘንድ ማሉልኝ፤ ለዚህም መተማመኛ የሚሆን ምልክት ስጡኝ። አባቴንና እናቴን፥ ወንድሞቼን፥ እኅቶቼንና የእነርሱን ቤተሰቦች ሁሉ ከሞት ለማዳን ቃል ግቡልኝ!” ሰዎቹም እንዲህ አሉአት፤ “እኛ በገባንልሽ ቃል መሠረት ባንፈጽም እግዚአብሔር በሞት ይቅጣን! እኛ ያደረግነውን ሁሉ ለማንም ባትነግሪ፥ እግዚአብሔር ይህቺን ምድር ለእኛ አሳልፎ በሚሰጠን ጊዜ ለአንቺ መልካም ነገር ለማድረግ ቃል እንገባለን።” ረዓብ የምትኖርበት ቤት ከከተማይቱ ቅጽር ግንብ ተጠግቶ በውስጥ በኩል የተሠራ ስለ ነበር ሰዎቹ በመስኮት በኩል ቊልቊል በተለቀቀ ገመድ ተንጠልጥለው ወደ ታች እንዲወርዱ አደረገች፤ እንዲህም ስትል መከረቻቸው፤ “ወደ ኮረብታማው አገር ሂዱ፤ ይህ ካልሆነ ግን የንጉሡ መልእክተኞች ሊያገኙአችሁ ይችላሉ፤ በዚያም እነርሱ እስኪመለሱ እስከ ሦስት ቀን ድረስ ተደብቃችሁ ቈዩ፤ ከዚያን በኋላ ጒዞአችሁን መቀጠል ትችላላችሁ።”