የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ኢያሱ 10

10
የፀሐይ መቆም
1ኢያሱ የዐይን ከተማ በጦርነት ከያዘ በኋላ በኢያሪኮና በንጉሥዋ ላይ ባደረገው ዐይነት በፍጹም የደመሰሳት መሆኑንና ንጉሥዋንም መግደሉን የኢየሩሳሌም ንጉሥ አዶኒጼዴቅ ሰማ፤ እንዲሁም የገባዖን ሰዎች ከእስራኤላውያን ጋር ስምምነት አድርገው በሰላም መኖራቸውን ተረዳ። 2ገባዖን በነገሥታት እንደሚተዳደሩት ከተሞች ትልቅና ከዐይ ትበልጥ የነበረች ከተማ ከመሆንዋም በላይ ሰዎችዋም ብርቱ ጦረኞች ስለ ነበሩ፥ አዶኒጼዴቅ በጣም ፈራ። 3ስለዚህ የኢየሩሳሌሙ ንጉሥ አዶኒጼዴቅ ሆሃም ተብሎ ለሚጠራው ለኬብሮን ንጉሥ፥ ፒራም ለተባለው ለያርሙት ንጉሥ፥ ያፊዓ ለተባለው ለላኪሽ ንጉሥና ደቢር ለተባለው ለዔግሎን ንጉሥ እንዲህ የሚል መልእክት ላከ፦ 4“ገባዖን ከኢያሱና ከእስራኤላውያን ጋር በሰላም አብሮ የመኖር ስምምነት ስላደረገች እርስዋን ለመውጋት መጥታችሁ እርዱኝ፤” 5እነዚህ የኢየሩሳሌም፥ የኬብሮን፥ የያርሙት፥ የላኪሽና የዔግሎን ገዢዎች አምስቱ አሞራውያን ነገሥታት ሠራዊታቸውን አስተባብረው፥ የጦር ግንባር በመፍጠር፥ ገባዖንን ከበው አደጋ ጣሉባት።
6የገባዖን ሰዎችም ሰፈሩን በጌልገላ አድርጎ ወደነበረው ወደ ኢያሱ እንዲህ ሲሉ መልእክት ላኩበት፦ “በተራራማው አገር የሚኖሩት የአሞራውያን ነገሥታት ሁሉ እኛን ሊወጉን ስለ ተባበሩብን እኛ አገልጋዮችህን ችላ አትበል! በቶሎ ወደ እኛ ወጥተህ እርዳንና አድነን!”
7ስለዚህም ኢያሱና መላው ሠራዊት፥ ምርጥ የሆኑት ወታደሮች ጭምር ከጌልጌላ ወጥተው ሄዱ፤ 8እግዚአብሔርም ኢያሱን “እነርሱን አትፍራቸው፤ እኔ አንተን በእነርሱ ላይ ድልን አቀዳጅሃለሁ፤ ከእነርሱ አንድም የሚቋቋምህ አይኖርም” አለው። 9ኢያሱም ሌሊቱን ሙሉ ከጌልጌላ ወደ ገባዖን ሲገሠግሥ ዐድሮ በአሞራውያን ላይ ድንገተኛ አደጋ ጣለባቸው። 10እግዚአብሔርም በእስራኤል ሠራዊት ፊት አሞራውያን በድንጋጤ እንዲሸበሩ አደረገ፤ እስራኤላውያንም እነርሱን በገባዖን ዐረዱአቸው፤ የቀሩትንም በቤትሖሮን በኩል እስከ ተራራው መተላለፊያ ቊልቊለት እስከ ዐዜቃና እስከ ማቄዳ ድረስ አሳደዱአቸው። 11አሞራውያን በመተላለፊያው ቊልቊለት ከእስራኤላውያን ሠራዊት በሚሸሹበት ጊዜ፥ እግዚአብሔር እስከ ዐዜቃ ድረስ ከሰማይ ታላላቅ የበረዶ ድንጋይ አወረደባቸው፤ ስለዚህም እስራኤላውያን ከገደሉአቸው ይልቅ በበረዶው ድንጋይ የሞቱት እጅግ ብዙዎች ነበሩ።
12እግዚአብሔር አሞራውያንን ለእስራኤላውያን አሳልፎ በሰጠበት ቀን ኢያሱ ከእግዚአብሔር ጋር ተነጋገረ፤ እርሱም በእስራኤል ፊት እንዲህ አለ፦ “ፀሐይ በገባዖን፥ ጨረቃም በኤሎን ሸለቆ ላይ ይቁሙ” አለ።
13ስለዚህም የእስራኤል ሕዝብ ጠላቶቻቸውን እስኪበቀሉ ድረስ ፀሐይ ቆመ፤ ጨረቃም ካለችበት ሳትንቀሳቀስ ቈየች፤ ይህም በያሻር መጽሐፍ ተጽፎ ይገኛል። ሳይንቀሳቀስ በሰማይ መካከል ቆመ፤ ቀኑንም ሙሉ ሳይጠልቅ ቈየ፤ #2ሳሙ. 1፥18። 14እግዚአብሔር የሰውን ቃል የሰማበት፥ እንደዚያ ያለ ቀን፥ ከዚያም በፊት ሆነ ከዚያ ወዲህ ታይቶ አይታወቅም፤ በእርግጥም እግዚአብሔር ከእስራኤል ጐን ተሰልፎ ይዋጋላቸው ነበር።
15ከዚህ በኋላ ኢያሱና ሠራዊቱ በጌልገላ ወደ ነበረው ሰፈር ተመለሱ።
ኢያሱ አምስቱን አሞራውያን ነገሥታት መግደሉ
16አምስቱ አሞራውያን ነገሥታትም አምልጠው በማቄዳ ዋሻ ተደብቀው ነበር፤ 17እነዚህም አምስቱ ነገሥታት በማቄዳ ዋሻ ውስጥ ተደብቀው መገኘታቸው ለኢያሱ ተነገረው። 18ኢያሱም እንዲህ ሲል ትእዛዝ ሰጠ፤ “ታላላቅ ድንጋዮች አንከባላችሁ የዋሻውን በር ዝጉ፤ በዚያም ዘብ ጠባቂ አቁሙበት፤ 19እናንተ ግን በዚያ አትቈዩ፤ ጠላትን እያሳደዳችሁ ከኋላ በኩል አደጋ መጣላችሁን ቀጥሉ፤ ሸሽተው ወደ ከተሞቻቸው እንዲገቡ መንገድ አትስጡአቸው! አምላካችሁ እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ድልን ያቀዳጃችኋልና።” 20ጥቂቶች ብቻ አምልጠው ወደ የከተሞቻቸው ምሽጎች ገብተው ከሞት ለመትረፍ ቢችሉም እንኳ ኢያሱና የእስራኤል ሰዎች ሁሉንም ዐረዱአቸው። 21ከዚህ በኋላ የኢያሱ ሰዎች ሁሉ በሰላም ተመልሰው እርሱ ወደ ሰፈረበት ወደ ማቄዳ መጡ።
ከዚህም የተነሣ በምድሪቱ በእስራኤላውያን ላይ ደፍሮ ቃል የሚናገር እንኳ አልነበረም።
22ከዚህም በኋላ ኢያሱ፦ “የዋሻውን በር ከፍታችሁ በማውጣት እነዚያን አምስት ነገሥታት ወደ እኔ አምጡ” ሲል ትእዛዝ ሰጠ፤ 23ስለዚህም ዋሻው ተከፍቶ እነዚያ አምስቱ የኢየሩሳሌም፥ የኬብሮን፥ የያርሙት፥ የላኪሽና የዔግሎን ነገሥታት እንዲወጡ ተደረገ፤ 24ወደ ኢያሱም አመጡአቸው፤ ኢያሱም የእስራኤልን ሰዎች ሁሉ ወደ እርሱ ጠራ፤ ከእርሱ ጋር የዘመቱት የጦር መኰንኖችም መጥተው እግራቸውን በነገሥታቱ አንገት ላይ እንዲያደርጉ ትእዛዝ ሰጠ፤ እነርሱም እንደ ታዘዙት አደረጉ። 25ኢያሱም ለጦር መኰንኖቹ እንዲህ አለ፤ እግዚአብሔር ጦርነት በምትገጥሙአቸው በጠላቶቻችሁ ሁሉ ላይ ልክ እንደዚህ ስለሚያደርግ አትፍሩ አይዞአችሁ፤ ቆራጥነትና ድፍረት ይኑራችሁ። 26ከዚህም በኋላ ኢያሱ አምስቱን ነገሥታት ገድሎ በአምስት ዕንጨት ላይ ሰቀላቸው፤ ሬሳቸውም እስከ ምሽት ድረስ በዚያው ዋለ። 27ፀሐይም ስትጠልቅ የነዚያ ነገሥታት ሬሳ ከየተሰቀለበት እንጨት እንዲወርድና ቀድሞ ተደብቀው ወደነበሩበት ዋሻ ውስጥ እንዲጣል ኢያሱ ትእዛዝ ሰጠ፤ ታላላቅ ድንጋዮችንም አንከባለው የዋሻውን ደጃፍ ገጠሙት፤ እስከ አሁን በዚያ ይገኛል።
ኢያሱ ጦርነቱን መቀጠሉ
28በዚያን ቀን ኢያሱ ማቄዳን ያዘ፤ ንጉሥዋንም በሰይፍ ገደለ፤ በከተማይቱ የነበሩትን ሰዎች ሁሉ አንድም ሳያስቀር ፈጀ፤ በማቄዳም ንጉሥ ላይ ያደረገው ቀድሞ በኢያሪኮ ንጉሥ ላይ ባደረገው ዐይነት ነው።
29ከዚህም በኋላ ኢያሱና ሠራዊቱ ከማቄዳ ሄደው በሊብና ላይ አደጋ ጣሉባት፤ 30እግዚአብሔርም በርስዋና በንጉሥዋ በእስራኤል ላይ ለእስራኤላውያን ድልን ሰጣቸው፤ ኢያሱም ከተማይቱንና በእርስዋ ያሉትን ሰዎች አጠፋ፤ በንጉሥዋም ላይ በኢያሪኮ ንጉሥ ላይ እንዳደረገው አደረገበት።
31ከዚህ በኋላ ኢያሱና ሠራዊቱ ከሊብና ወደ ላኪሽ ዘምተው ከበባ በማድረግ፥ አደጋ ጣሉባት፤ 32እግዚአብሔርም ጦርነቱ በተጀመረ በሁለተኛው ቀን ለእስራኤላውያን በላኪሽ ላይ ድልን ሰጣቸው፤ በሊብና ባደረጉትም ዐይነት በከተማይቱ ያገኙትን ሰው ሁሉ በሰይፍ ፈጁ፤ 33በዚህ ጊዜ የጌዜር ንጉሥ ሆራም ላኪሽን ለመርዳት መጥቶ ነበር፤ ነገር ግን ኢያሱ እርሱንና ሠራዊቱን ድል አደረገ፤ ከእነርሱም በሕይወት የተረፈ አንድ እንኳ አልነበረም።
34ቀጥሎም ኢያሱና ሠራዊቱ ከላኪሽ ወደ ዔግሎን ዘምተው ከበባ በማድረግ አደጋ ጣሉበት፤ 35በዚያኑም ዕለት ከተማይቱን ያዙ፤ በሰይፍ መቱአት፤ ልክ በላኪሽ እንዳደረጉት ዐይነት ያገኙትን ሰው ሁሉ ገደሉ።
36ከዚህ በኋላ ኢያሱና ሠራዊቱ ከዔግሎን ወጥተው በኬብሮን ላይ አደጋ ጣሉባት። 37እርስዋንም ይዘው ንጉሡን፥ በከተማይቱና በአካባቢዋም የገጠር ከተሞች ያገኙትን ሁሉ ገደሉ፤ ኢያሱም ልክ በዔግሎን ባደረገው ዐይነት ከተማይቱ እንድትደመሰስ ፈረደባት፤ በእርስዋም ውስጥ በሕይወት የተረፈ አንድም አልነበረም።
38ከዚህ በኋላ ኢያሱና ሠራዊቱ ወደ ደቢር ተመልሰው በመዝመት አደጋ ጣሉባት፤ 39ንጉሡንና ከተማዎቹን ሁሉ ያዙ፤ የከተማዎቹንም ሰዎች በሰይፍ ፈጁ፤ ልክ በኬብሮን፥ በሊብናና በነገሥታቱ ላይ እንዳደረጉት በዶቢርም አንድ ሰው እንኳ ሳይተርፋቸው በዚያ ያሉትን ሰዎች ሁሉ ፈጁ።
40በዚህ ዐይነት ኢያሱ ምድሪቱን በሙሉ፥ የተራራማውን አገር፥ ኔጌብን፥ የተራራውን ቊልቊለትና ነገሥታቱን ሁሉ ያዘ፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ሁሉንም ፈጀ እንጂ አንድ ሰው እንኳ በሕይወት እንዲኖር አላስተረፈም። 41ኢያሱም ከቃዴስ በርኔ እስከ ጋዛ የጎሼንን አካባቢ ሁሉ ጨምሮ፥ እስከ ገባዖን ድረስ ወግቶ ድል አደረገ። 42ኢያሱ እነዚህን ነገሥታትና ግዛቶቻቸውን ሁሉ በአንድ ዘመቻ ድል ያደረገው የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ለእስራኤል ይዋጋላቸው ስለ ነበረ ነው። 43ከዚህም በኋላ ኢያሱና ሠራዊቱ በጌልገላ ወደነበረው ሰፈር ተመለሱ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ