ትንቢተ ዮናስ 4:5-11

ትንቢተ ዮናስ 4:5-11 አማ05

ዮናስም ከከተማይቱ ወጥቶ ከከተማይቱም በስተ ምሥራቅ በኩል ዳስ በመሥራት ከጥላው ሥር ተቀመጠ፤ በዚያም ሆኖ በነነዌ ላይ የሚደርሰውን ነገር ይጠባበቅ ነበር። ጥላ በማግኘት ከፀሐይ ግለት እንዲድን እግዚአብሔር አምላክ አንድ የቅል ተክል አብቅሎ ቅጠሎችዋ ከዮናስ ራስ በላይ እንዲሆኑ አደረገ፤ ዮናስም ከቅሉ ሐረግ ጥላ በማግኘቱ እጅግ ተደሰተ። ነገር ግን በማግስቱ ጠዋት እግዚአብሔር አንድ ትል አዘጋጀ፤ ትልዋም ቅሊቱን በላች፤ እርሷም ደረቀች። ፀሐይ ከወጣ በኋላ እግዚአብሔር የሚያቃጥል የምሥራቅ ነፋስ ላከ፤ የፀሐዩም ሐሩር ራሱን ስላቃጠለው ዮናስ ተዝለፈለፈ፤ ሞትንም በመመኘት “ከመኖር ይልቅ መሞት ይሻለኛል” አለ። እግዚአብሔርም “ስለዚህች ቅል ልትበሳጭ ይገባሃልን?” አለው። ዮናስም “በእርግጥ መበሳጨት ይገባኛል፤ እንዲያውም በንዴት እስከምሞት ድረስ መበሳጨት አለብኝ!” አለ። እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፦ “አንተ በአንድ ቀን በቅላ፥ በአንድ ቀን ለደረቀች፥ እንዲያውም ላልደከምክባትና ላላሳደግሃት ተክል ይህን ያኽል አዝነሃል! ነነዌ ክፉና ደጉን የማይለዩ ከአንድ መቶ ኻያ ሺህ ሕዝብ በላይ የሚኖሩባት ከተማ ነች፤ ብዙ እንስሶችም አሉባት፤ ታዲያ እኔ ለዚህች ታላቂቱ ከተማ አልራራምን?”