ትንቢተ ዮናስ 3
3
የዮናስ ለእግዚአብሔር መታዘዝ
1እግዚአብሔር ለሁለተኛ ጊዜ ዮናስን እንዲህ አለው፦ 2“ተነሥተህ ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፤ እኔም የምነግርህን ቃል ለሕዝቡ ዐውጅ።” 3ዮናስም ለእግዚአብሔር በመታዘዝ ተነሥቶ ወደ ነነዌ ሄደ፤ ነነዌ እጅግ ታላቅ ከተማ ከመሆንዋ የተነሣ ከተማዋን በመላ ለማዳረስ ሦስት ቀን ይፈጅ ነበር። 4ዮናስ ወደ ከተማይቱ ገብቶ ጒዞውን ጀመረ፤ የአንድ ቀን መንገድም እንደ ሄደ “ነነዌ በአርባ ቀን ውስጥ ትደመሰሳለች!” ብሎ ዐወጀ። #3፥4 አርባ፦ ዕብራይስጡ “አርባ ቀን” ሲል የሰባ ሊቃናት ትርጒም ሦስት ቀን ይላል።
5የነነዌ ሕዝብ የእግዚአብሔርን ቃል አመኑ፤ ጾምም ዐወጁ፤ መጸጸታቸውንም ለመግለጥ ከታላላቅ ጀምሮ እስከ ታናናሽ ድረስ ሁሉም ማቅ ለበሱ። #ማቴ. 12፥41፤ ሉቃ. 11፥32።
6የነነዌ ንጉሥ ይህን ነገር በሰማ ጊዜ፥ ከዙፋኑ ወረደ፤ ልብሰ መንግሥቱንም በማውለቅ ማቅ ለብሶ ዐመድ ላይ ተቀመጠ። 7ለነነዌም ሕዝብ እንዲህ ሲል ዐዋጅ አስነገረ፥ “ከንጉሡና ከመኳንንቱ በተላለፈው ትእዛዝ መሠረት፥ ማንም ሰው ወይም እንስሳ፥ የከብትም ሆነ የበግ መንጋ አንዳች ምግብ አይቅመሱ፤ ውሃም አይጠጡ፤ 8ሰዎችም ሆኑ እንስሶች ማቅ ይልበሱ፤ እያንዳንዱ ሰው ከልብ ወደ እግዚአብሔር ይጩኽ፤ መጥፎ ጠባዩንና የግፍ ሥራውን ይተው። 9እኛ ከጥፋት እንድንድን ምናልባት እግዚአብሔር ራርቶልን ከሚያስፈራው ቊጣው ይመለስ እንደ ሆነ ማን ያውቃል?”
10እግዚአብሔር የነነዌ ሰዎች ያደረጉትንና ከክፉ መንገዳቸው መመለሳቸውን ተመለከተ፤ ስለዚህም ራርቶላቸው በእነርሱ ላይ ሊያመጣ የነበረውን ቅጣት አልፈጸመም።
Currently Selected:
ትንቢተ ዮናስ 3: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997