የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢዩኤል 1

1
የአንበጣ መንጋ ያስከተለው ጥፋት
1ለባቱኤል ልጅ ለኢዩኤል ከእግዚአብሔር የመጣለት የትንቢት ቃል ይህ ነው፦
2እናንተ ሽማግሌዎች ይህን ስሙ!
በይሁዳም ምድር የምትኖሩ ሁሉ ይህን አድምጡ!
ለመሆኑ ይህን የመሰለ ነገር በዘመናችሁ
ወይም በቀድሞ አባቶቻችሁ ዘመን ተደርጎ ያውቃልን?
3ይህን ነገር ለልጆቻችሁ ንገሩ፤
ልጆቻችሁም ለልጆቻቸው ይንገሩ፤
እነርሱ ደግሞ ለሚከተለው ትውልድ ይንገሩ።
4ከተምች መንጋ የተረፈውን ሰብል፥
የሚርመሰመስ የአንበጣ መንጋ በላው፤
ከዚያ የተረፈውን እንደ ውሽንፍር የሚገርፍ
የአንበጣ መንጋ አጠፋው፤
ከዚያም የተረፈውን ኲብኲባ በላው።
5ከእንግዲህ ወዲህ አዲስ የወይን ጠጅ በአፋችሁ ስለማትቀምሱ፥
እናንተ ሰካራሞች ከእንቅልፋችሁ ነቅታችሁ አልቅሱ፤
እናንተም የወይን ጠጅ መጠጣት የምታዘወትሩ
ምርር ብላችሁ አልቅሱ።
6ስፍር ቊጥር የሌለው የአንበጣ መንጋ፥
እንደ ወራሪ ጦር በምድሬ ላይ መጥቶአል፤
ጥርሱ እንደ አንበሳ ጥርስ ነው፤
መንጋጋውም እንደ ሴት አንበሳ መንጋጋ ነው። #ራዕ. 9፥8።
7የወይን ተክሎቼን ሁሉ አጠፋ፤
የበለስ ዛፎቼንም ቈራረጠ፤
ቅርንጫፎቻቸው ነጭ ሆነው እስከሚታዩ ድረስ፥
ቅርፊቱን ልጦ ጣለ።
8ስለዚህ እጮኛዋ ስለ ሞተባት
ማቅ ለብሳ እንደምታለቅስ
ልጃገረድ እናንተም አልቅሱ።
9በእግዚአብሔር ቤት መባ ሆኖ የሚቀርብ
እህልም ሆነ የወይን ጠጅ በመታጣቱ፥
የእግዚአብሔር አገልጋዮች የሆኑት ካህናት ያለቅሳሉ።
10እርሻዎች ባዶአቸውን ቀርተዋል፤
እህል ጠፍቶአል፤
የወይን ተክሎች ደርቀዋል፤
ዘይትም ጠፍቶአል፤
ስለዚህ ምድር ታለቅሳለች።
11ስንዴውና ገብሱ፥ ሌላውም መከር ሁሉ ስለ ጠፋ፥
እናንተ ገበሬዎች እዘኑ፤
እናንተም የወይን ተክል ባለቤቶች አልቅሱ።
12የወይን ተክሎችና የበለስ ዛፎች ጠውልገዋል፤
ሮማኑ፥ ተምሩና እንኰዩ፥ ሌሎችም የፍራፍሬ ዛፎች ሁሉ ደርቀዋል፤
በዚህም ምክንያት በእርግጥ ደስታ ከሰው ልጆች ርቆአል።
13ለአምላካችሁ የምታቀርቡት የእህልም ሆነ የወይን ጠጅ መባ ስለሌለ
እናንተ የአምላኬ አገልጋዮች የሆናችሁ ካህናት!
ኑና ማቅ ለብሳችሁ ሌሊቱን ሁሉ አልቅሱ!
እናንተም በመሠዊያው ላይ የምታገለግሉ
ዋይ! ዋይ! በሉ።
14የተለየ የጾም ቀን ዐውጁ!
መንፈሳዊ ስብስባ ጥሩ!
ሽማግሌዎችንና ሌሎችንም የአገሪቱን ኗሪዎች ሁሉ
ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ቤት ሰብስቡ፤
በዚያም ወደ እግዚአብሔር ጩኹ።
15ወዮ! የጌታ ቀን ቀርቦአል!
ሁሉን ቻይ እግዚአብሔር ጥፋትን የሚያመጣበት ቀን ደርሶአል።
ስለዚያ ቀን ወዮ! #ኢሳ. 13፥6።
16እህል ከዐይናችን
ደስታና እልልታ ከአምላካችን ቤተ መቅደስ፥
ፈጽሞ ጠፍቶአል።
17የተዘራው እህል ሁሉ በዐፈር ውስጥ በስብሶ ቀርቶአል፤
እህል በመታጣቱ የእህል ማከማቻዎች ሁሉ ባዶ ሆነዋል፤
ጐተራዎችም ፈራርሰዋል።
18የግጦሽ ሣር በማጣት ከብቶች ያላዝናሉ፤
የበጎች መንጋ ሳይቀሩ ተርበው በብርቱ ሥቃይ ላይ ይገኛሉ።
19እግዚአብሔር ሆይ! የሜዳውን ሣር ሁሉ እሳት ስለ በላው፥
የዱሩንም ዛፍ እሳት ስለ አቃጠለው
እኔ ወደ አንተ እጮኻለሁ።
20ወንዞች ስለ ደረቁባቸው፥
የሜዳውም ሣር ሁሉ ስለ ተቃጠለባቸው፥
የዱር አራዊት እንኳ ወደ አንተ ይጮኻሉ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}