“ቈንጆይቱን በፍትወት ዐይን እንዳልመለከት፥ ከዐይኔ ጋር ቃል ኪዳን ገብቼአለሁ። “ከላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተወሰነው የሰው ዕድል ፈንታ ምንድን ነው? በአርያም ካለው ሁሉን ከሚችል አምላክ፥ የተሰጠው ድርሻስ ምንድን ነው? በክፉ ሰው ላይ መዓት፥ በበደለኛ ሰውም ላይ ጥፋት፥ የታወቀ አይደለምን? እግዚአብሔር የማደርገውን ሁሉ አያይምን? እርምጃዎቼንስ አይቈጣጠርምን? “ሐሰት ተናግሬ እንደ ሆነ፥ ሰውንም አታልዬ እንደ ሆነ፥ እግዚአብሔር በትክክለኛ ሚዛን ይመዝነኝ፤ በቅንነት መጽናቴንም ይወቅ። ከትክክለኛው መንገድ ወጥቼ እንደ ሆነ፥ ዐይኔ ያየውን ሁሉ ልቤ ጐምጅቶ እንደ ሆነ፤ እጄም በኃጢአት አድፎ እንደ ሆነ፥ እኔ የዘራሁትን ሌላ ሰው ይብላው፤ ቡቃያዬም ሁሉ ተነቃቅሎ ይጥፋ። ልቤ በሌላ ሴት ፍቅር ተማርኮ እንደ ሆነ፥ የጐረቤቴንም ሚስት ለማግኘት በደጃፉ አድብቼ እንደ ሆነ፥ ሚስቴ ለሌላ ሰው ፈጫይ ሆና ታገልግል፤ መኝታዋም ከሌሎች ወንዶች ጋር ይሁን። ይህም ተግባር በሕግ ፊት የሚያስቀጣ፥ ታላቅ ወንጀል ነው። ይህ ኃጢአት እንደ እሳት አቃጥሎ የሚያጠፋ ስለ ሆነ እኔ ይህን ብሠራ ኖሮ ሀብቴን ሁሉ ባወደመው ነበር። “ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮቼ አቤቱታ አቅርበውልኝ አቤቱታቸውን ሳልቀበል ቀርቼ እንደ ሆነ፥ በእግዚአብሔር ፊት ለፍርድ በቆምኩ ጊዜ ምን ይበጀኝ ይሆን? በፍርድ በሚመረምረኝስ ጊዜ ለሚያቀርብልኝ ጥያቄ ምን መልስ መስጠት እችል ይሆን? በማሕፀን ውስጥ እኔን የፈጠረ አገልጋዮቼንስ የፈጠረ አይደለምን? ሁላችንንስ በማሕፀን ውስጥ የሠራ፥ እርሱ አይደለምን? “ድኾች የሚለምኑትን ከልክዬ አላውቅም፤ ባሎቻቸው የሞቱባቸውንም ሴቶች ከማጽናናት አልተቈጠብኩም። የሙት ልጆች እየራባቸው ምግቤን ብቻዬን አልበላሁም። ነገር ግን ከወጣትነቴ ጀምሬ እንደ አባት ሆኜላቸዋለሁ፤ በሕይወቴ ዘመኔ ሁሉ ባልዋ የሞተባትን ረድቼአለሁ። አንድ ሰው ከልብስ እጦት ወይም አንድ ችግረኛ የሚለብሰው አጥቶ ራቁቱን ሆኖ ባይ፥ ከበጎቼ ጠጒር የተሠራ ልብስ አልብሼው ሞቆት ሳይመርቀኝ የቀረበት ጊዜ የለም። በፍርድ ሸንጎ ተሰሚነት ያለኝ መሆኔን በማወቄ በሙት ልጅ ላይ እጄን አንሥቼ አላውቅም። ይህን ሁሉ ሳላደርግ ቀርቼ ከሆነ ክንዴ ከትከሻዬ ይውለቅ፤ ከመገናኛውም ተሰብሮ ይለይ፥ የእግዚአብሔርን መቅሠፍት እፈራለሁ፤ ከግርማውም አስፈሪነት የተነሣ በፊቱ መቆም አልችልም። “እምነቴን በሀብት ላይ አድርጌ አላውቅም፤ ወይም ንጹሕ ወርቅንም መታመኛዬ አላደረግሁም። ‘ሀብቴ በዝቷል፥ በብልጽግናዬም ብዙ ገንዘብ አግኝቼአለሁ’ ብዬ ተደስቼ አላውቅም። የፀሐይን ማሸብረቅ፥ የጨረቃን መድመቅ ተመልክቼ፥ ልቤ በስውር ለእነርሱ አልተማረከም እጄንም ዘርግቼ በመሳም አክብሮት አላቀረብኩላቸውም። ይህን ማድረግ በላይ ለሚገኘው አምላክ እምነተቢስነት ስለ ሆነ፥ እነዚህ ድርጊቶች የሞት ፍርድ የሚያመጡ ኃጢአቶች ናቸው። “በሚጠሉኝ ሰዎች ውድቀት አልተደሰትኩም፤ ክፉ ነገርም ሲደርስባቸው ሐሴት አላደረግሁም ‘ጠላቶቼ ይጥፉ’ ብዬ በመራገም ኃጢአት ከቶ አልሠራሁም። በእርግጥ ቤተሰቦቼ ‘ከእርሱ ዘንድ ምግብ በልቶ ያልጠገበ ከቶ ማነው?’ ብለው ይመሰክራሉ። ቤቴን ለመንገደኞች ክፍት አደርግ ስለ ነበረ፥ በውጪ የሚያድር እንግዳ ከቶ አልነበረም። “በደሌን በውስጤ አልሸሸግሁም እንደ ሌሎች ሰዎች ኃጢአቴንም አልሰወርኩም። የሕዝቡ ብዛት አስፈርቶኝና፥ የቤተሰብም ነቀፋ አስደንግጦኝ ጸጥ ብዬ በቤት ውስጥ የተደበቅኹበት ጊዜ የለም። “ምነው የሚሰማኝ ባገኘሁ! መከላከያዬን አቀርባለሁ፤ ሁሉን ቻይ አምላክ ይመልስልኝ! ምነው ከሳሼም የክሱን ዝርዝር በጽሑፍ አቅርቦልኝ ባየሁት!
መጽሐፈ ኢዮብ 31 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ኢዮብ 31:1-35
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች