የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ኢዮብ 31:1-12

መጽሐፈ ኢዮብ 31:1-12 አማ05

“ቈንጆይቱን በፍትወት ዐይን እንዳልመለከት፥ ከዐይኔ ጋር ቃል ኪዳን ገብቼአለሁ። “ከላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተወሰነው የሰው ዕድል ፈንታ ምንድን ነው? በአርያም ካለው ሁሉን ከሚችል አምላክ፥ የተሰጠው ድርሻስ ምንድን ነው? በክፉ ሰው ላይ መዓት፥ በበደለኛ ሰውም ላይ ጥፋት፥ የታወቀ አይደለምን? እግዚአብሔር የማደርገውን ሁሉ አያይምን? እርምጃዎቼንስ አይቈጣጠርምን? “ሐሰት ተናግሬ እንደ ሆነ፥ ሰውንም አታልዬ እንደ ሆነ፥ እግዚአብሔር በትክክለኛ ሚዛን ይመዝነኝ፤ በቅንነት መጽናቴንም ይወቅ። ከትክክለኛው መንገድ ወጥቼ እንደ ሆነ፥ ዐይኔ ያየውን ሁሉ ልቤ ጐምጅቶ እንደ ሆነ፤ እጄም በኃጢአት አድፎ እንደ ሆነ፥ እኔ የዘራሁትን ሌላ ሰው ይብላው፤ ቡቃያዬም ሁሉ ተነቃቅሎ ይጥፋ። ልቤ በሌላ ሴት ፍቅር ተማርኮ እንደ ሆነ፥ የጐረቤቴንም ሚስት ለማግኘት በደጃፉ አድብቼ እንደ ሆነ፥ ሚስቴ ለሌላ ሰው ፈጫይ ሆና ታገልግል፤ መኝታዋም ከሌሎች ወንዶች ጋር ይሁን። ይህም ተግባር በሕግ ፊት የሚያስቀጣ፥ ታላቅ ወንጀል ነው። ይህ ኃጢአት እንደ እሳት አቃጥሎ የሚያጠፋ ስለ ሆነ እኔ ይህን ብሠራ ኖሮ ሀብቴን ሁሉ ባወደመው ነበር።