መጽሐፈ ኢዮብ 27
27
ኢዮብ
1ኢዮብም ንግግሩን በመቀጠል እንዲህ አለ፦
2“ትክክለኛ ፍርድ በመከልከል፥
ሕይወቴን እጅግ መራራ ባደረገው ሁሉን በሚችል በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ።
3እግዚአብሔር የሕይወት እስትንፋስ ሰጥቶኝ
እስከ አለሁ ድረስ
4ከቶ ክፉ ቃል ከአፌ አይወጣም፤
በአንደበቴም ሐሰት አልናገርም።
5እናንተ የተናገራችሁት ሁሉ ትክክል ነው ብዬ በፍጹም አልቀበልም፤
እስከምሞትበት ቀን ድረስ በቅንነት መጽናቴን አልተውም።
6“በእውነተኛነቴ እጸናለሁ፤ እርሱንም አልተውም፤
በሕይወት በምኖርበት ዘመን ሁሉ ኅሊናዬ በዚህ ነገር አይወቅሰኝም።
7“ጠላቶቼ እንደ ኃጢአተኞች፥
ተቃዋሚዎቼም እንደ ግፈኞች ይፈረድባቸው።
8እግዚአብሔር ነፍሳቸውን ከሥጋቸው በመለየት ዕድሜአቸውን ባሳጠረ ጊዜ፥
እግዚአብሔርን የሚክዱ ሰዎች ምን ተስፋ ይኖራቸዋል?
9መከራ በሚመጣባቸው ጊዜ እግዚአብሔር ጩኸታቸውን ይሰማልን?
10ሁሉን በሚችል አምላክ ይደሰታሉን?
በየጊዜውስ የእግዚአብሔርን ስም ይጠራሉን?
11“የእግዚአብሔር ኀይል ምን ያኽል ታላቅ እንደ ሆነ አስተምራችኋለሁ፤
ሁሉን የሚችል አምላክ ያቀደውንም አልሸሽግባችሁም፤
12እናንተም እኮ ይህን ሁሉ ታውቃላችሁ፤
ታዲያ ይህን ከንቱ ነገር ለምን ትናገራላችሁ?”
13“እነሆ ሁሉን የሚችል አምላክ
ክፉ ሰውንና ግፈኛን የሚቀጣው በዚህ ዐይነት ነው፤
14ልጆቹ ቢበዙ በጦርነት ያልቃሉ፤
ዘሮቹም ምግብ አጥተው ይራባሉ።
15ከዚህ የተረፉትም በበሽታ ያልቃሉ፤
መበለቶቻቸው እንኳ አያለቅሱላቸውም።
16ክፉ ሰው ብርን እንደ ዐፈር ሊያጋብስ፥
ልብስንም እንደ ሸክላ ሊከምር ይችላል፤
17ዳሩ ግን ክፉ ሰው የሰበሰበውን ልብስ ጻድቅ ይለብሰዋል፤
ያካበተውንም ብር ንጹሖች ይካፈሉታል።
18የሚሠራው ቤት እንደ ሸረሪት ድርና
እንደ ሰብል ጠባቂ ጎጆ ይፈራርሳል።
19ክፉ ሰው ለመጨረሻ ጊዜ ሀብታም ሆኖ ይተኛል፤
ሲነቃ ግን ሀብቱ ሁሉ ጠፍቶአል።
20ድንጋጤ እንደ ጐርፍ በድንገት ይደርስበታል፤
በሌሊትም ዐውሎ ነፋስ ይነጥቀዋል።
21የምሥራቅ ነፋስ ከመኖሪያ ቤቱ ጠራርጎ ይወስደዋል፤
22ሸሽቶ ለማምለጥ ቢሞክርም
ነፋሱ ያለ ርኅራኄ በእርሱ ላይ ያይልበታል፤
23ነፋሱ በእርሱ ላይ አጨበጨበ፤
በአለበትም ቦታ ሆኖ አፏጨበት።
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 27: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997