የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የዮሐንስ ወንጌል 8:1-11

የዮሐንስ ወንጌል 8:1-11 አማ05

ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ወደ ደብረ ዘይት ሄደ። በማግስቱም ጠዋት በማለዳ ወደ ቤተ መቅደስ ተመልሶ መጣ፤ ሕዝቡም ሁሉ ወደ እርሱ መጡ፤ እርሱም ተቀምጦ ያስተምር ነበር። የሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን ስታመነዝር የተያዘች ሴት አመጡና በሕዝቡ መካከል አቆሙአት። ኢየሱስንም እንዲህ አሉት፦ “መምህር ሆይ፥ እነሆ፥ ይህች ሴት ስታመነዝር ተይዛለች፤ እንዲህ ዐይነትዋ ሴት በድንጋይ ተወግራ እንድትሞት ሙሴ በሕጋችን አዞናል፤ አንተስ ስለ እርስዋ ምን ትላለህ?” ይህንንም ያሉት በእርሱ ላይ የክስ ምክንያት እንዲያገኙ ሊፈትኑት ፈልገው ነበር፤ ኢየሱስ ግን ጐንበስ ብሎ በጣቱ በመሬት ላይ ይጽፍ ጀመር። ደጋግመው በጠየቁት ጊዜ ቀና አለና፥ “ከእናንተ መካከል ኃጢአት የሌለበት የመጀመሪያውን ድንጋይ በእርስዋ ላይ ይጣል!” አላቸው። ከዚህም በኋላ እንደገና ጐንበስ ብሎ በመሬት ላይ ጻፈ። እነርሱም ይህን በሰሙ ጊዜ ከሽማግሌዎች ጀምሮ ሁሉም አንድ በአንድ ከዚያ ሄዱ፤ ስለዚህ ኢየሱስ በመካከል ቆማ ከነበረችው ሴት ጋር ብቻውን ቀረ። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ቀና ብሎ፥ “አንቺ ሴት ከሳሾችሽ የት አሉ? የፈረደብሽ ማንም የለምን?” አላት። እርስዋም “ጌታ ሆይ! ማንም የለም” አለች። ኢየሱስም “እኔም አልፈርድብሽም፤ ሂጂ፤ ዳግመኛ ኃጢአት አትሥሪ” አላት።