ከዚህ በኋላ የአይሁድ በዓል ስለ ነበረ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ። በኢየሩሳሌም በበጎች በር አጠገብ፥ በዕብራይስጥ ቋንቋ ቤተ ሳይዳ የሚባል አንድ የምንጭ ኲሬ ነበረ፤ በዙሪያውም አምስት ከላይ ክዳን ያላቸው መተላለፊያዎች ነበሩ። [በጣም ብዙ በሽተኞች፥ ዕውሮች አንካሶችና ሽባዎች በመተላለፊያዎቹ ተኝተው ነበር። እነዚህ የውሃውን መንቀሳቀስ ይጠባበቁ ነበር፤ አልፎ አልፎ የጌታ መልአክ ወደ ኲሬው ወርዶ ውሃውን ያናውጥ ነበር፤ ከውሃው መናወጥ በኋላ በመጀመሪያ ወደ ኲሬው የሚገባ ካደረበት ከማንኛውም በሽታ ይፈወስ ነበር።] በዚያም ሠላሳ ስምንት ዓመት ሙሉ የታመመ አንድ ሰው ነበረ። ኢየሱስ ይህን ሰው እዚያ ተኝቶ አየውና ከብዙ ጊዜ ጀምሮ መታመሙን ዐውቆ፥ “መዳን ትፈልጋለህን?” አለው። በሽተኛውም “ጌታ ሆይ! ውሃው በሚንቀሳቀስበት ጊዜ እኔን ወስዶ ወደ ኲሬው የሚያስገባኝ ሰው የለኝም፤ እኔ ልሄድ ስል ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል” አለው። ኢየሱስም “ተነሥ! አልጋህን ተሸከምና ሂድ!” አለው። ሰውየውም ወዲያውኑ ዳነ፤ አልጋውንም ተሸክሞ ሄደ። ይህም የሆነው በሰንበት ቀን ነበር፤ ስለዚህ የአይሁድ ባለሥልጣኖች ያንን የዳነውን ሰው “ዛሬ ሰንበት ስለ ሆነ አልጋህን እንድትሸከም ሕግ አይፈቅድልህም” አሉት። እርሱ ግን “ያዳነኝ ሰው አልጋህን ተሸክመህ ሂድ” ብሎኛል አላቸው። እነርሱም “አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ያለህ ማን ነው?” ሲሉ ጠየቁት። ሰውየው ግን ሕዝብ ስለ በዛና ኢየሱስም ከዚያ ራቅ ብሎ ስለ ሄደ ያዳነው ማን እንደ ሆነ አያውቅም ነበር። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ሰውየውን በቤተ መቅደስ አገኘውና “እነሆ፥ አሁን ድነሃል፤ ከዚህ የባሰ ነገር እንዳይደርስብህ ከእንግዲህ ወዲህ ኃጢአት አትሥራ” አለው። ሰውየውም ሄደና ያዳነው ኢየሱስ መሆኑን ለአይሁድ ባለሥልጣኖች ነገረ። ይህን ነገር በሰንበት ስላደረገ የአይሁድ ባለሥልጣኖች ኢየሱስን ያሳድዱት ጀመር። ኢየሱስ ግን “አባቴ ሁልጊዜ ይሠራል፤ እኔም እሠራለሁ” ሲል መለሰላቸው። ይህም አባባል የአይሁድን ባለሥልጣኖች ኢየሱስን እንዲገድሉት በይበልጥ አነሣሣቸው፤ ይህም የሆነው እርሱ ሰንበትን በመሻሩ ብቻ ሳይሆን “እግዚአብሔር አባቴ ነው” በማለት ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር ስለ አስተካከለ ነው። ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ አብ ሲሠራ ያየውን ከመሥራት በቀር ወልድ በራሱ ሥልጣን ምንም ሊሠራ አይችልም። አብ የሚያደርገውን ወልድም እንዲሁ ያደርጋል። አብ ወልድን ስለሚወድ የሚሠራውን ሁሉ ያሳየዋል፤ እናንተም እንድትደነቁ ከዚህ የበለጠ ሥራም ያሳየዋል። አብ የሞቱትን እንደሚያስነሣና ሕይወትን እንደሚሰጣቸው፥ ወልድም እንዲሁ ለፈለገው ሰው ሕይወትን ይሰጠዋል። አብ በማንም ላይ አይፈርድም፤ ነገር ግን ፍርድን ሁሉ ለወልድ ሰጥቶአል። ይህንንም ያደረገው ሰዎች ሁሉ አብን እንደሚያከብሩ፥ እንዲሁም ወልድን እንዲያከብሩ ነው፤ ወልድን የማያከብር፥ ወልድን የላከውን አብን አያከብርም። “እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ ቃሌን የሚሰማና በላከኝም የሚያምን የዘለዓለም ሕይወት አለው፤ እርሱ ከሞት ወደ ሕይወት የተሻገረ ስለ ሆነ አይፈረድበትም። እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ የሞቱ ሰዎች የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል፤ ጊዜውም አሁን ነው፤ የሚሰሙትም ሁሉ በሕይወት ይኖራሉ። አብ ራሱ የሕይወት ምንጭ እንዲሆን አድርጎታል። የሰው ልጅ በመሆኑም ፍርድ እንዲፈርድ ሥልጣን ሰጥቶታል። በዚህ ነገር አትደነቁ፤ በመቃብር ውስጥ ያሉት ሁሉ የእርሱን ድምፅ የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል። መልካም የሠሩ ከሞት ተነሥተው በሕይወት ይኖራሉ፤ ክፉ የሠሩ ግን ከሞት ተነሥተው ይፈረድባቸዋል። “እኔ በራሴ ሥልጣን ምንም ማድረግ አልችልም፤ ነገር ግን ከአብ የሰማሁትን እፈርዳለሁ፤ የላከኝን ፈቃድ እንጂ የራሴን ፈቃድ ስለማላደርግ ፍርዴ ትክክል ነው። “እኔ ስለ ራሴ ብመሰክር ምስክርነቴ እውነት አይደለም። ነገር ግን ስለ እኔ የሚመሰክር ሌላ አለ፤ እርሱም ስለ እኔ የሚመሰክረው ምስክርነት እውነት መሆኑን ዐውቃለሁ። እናንተ ወደ ዮሐንስ መልእክተኞች ልካችሁ ነበር፤ እርሱም ስለ እውነት መስክሮአል። ይህንንም ማለቴ እንድትድኑ ነው እንጂ እኔ የሰው ምስክርነት ስላስፈለገኝ አይደለም። ዮሐንስ እንደሚነድና እንደሚበራ መብራት ነበረ፤ እናንተም ለጥቂት ጊዜ በእርሱ ብርሃን ለመደሰት ፈለጋችሁ። እኔ ግን ከዮሐንስ ምስክርነት የበለጠ ምስክር አለኝ፤ ምስክሬም አባቴ እንድሠራው የሰጠኝ ሥራ ነው፤ ይህም የምሠራው ሥራ፥ አብ እንደ ላከኝ ስለ እኔ ይመሰክራል። የላከኝም አብ፥ ራሱ ስለ እኔ መስክሮአል፤ እናንተ ግን ድምፁን ከቶ አልሰማችሁም፤ መልኩንም ከቶ አላያችሁም። እርሱ የላከውን ስለማታምኑ የእርሱ ቃል በእናንተ ዘንድ አይኖርም። እናንተ በቅዱሳት መጻሕፍት የዘለዓለምን ሕይወት የምታገኙ ስለሚመስላችሁ እነርሱን ትመረምራላችሁ፤ እነርሱም ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው። ይሁን እንጂ እናንተ ሕይወትን ለማግኘት ወደ እኔ መምጣት አትፈልጉም። “እኔ ክብርን ከሰው አልፈልግም። እናንተ ከልባችሁ እግዚአብሔርን የማታፈቅሩ መሆናችሁን ዐውቃለሁ። እኔ በአባቴ ስም መጣሁ፤ እናንተ ግን አልተቀበላችሁኝም፤ ሌላ በራሱ ስም ቢመጣ ግን ትቀበሉታላችሁ። እናንተ እርስ በርሳችሁ ክብርን የምትፈልጉ ከአንዱ ከእግዚአብሔር የሚገኘውን ክብር ግን የማትፈልጉ፥ እንዴት ልታምኑ ትችላላችሁ? እኔ በአባቴ ፊት የምከሳችሁ አይምሰላችሁ፤ የሚከሳችሁ፥ ተስፋ የምታደርጉበት ሙሴ ነው። ሙሴን ብታምኑ ኖሮ እርሱ ስለ እኔ ጽፎአልና እኔንም ባመናችሁ ነበር። እርሱ የጻፈውን ካላመናችሁ ግን የእኔን ቃል እንዴት ታምናላችሁ?”
የዮሐንስ ወንጌል 5 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የዮሐንስ ወንጌል 5:1-47
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች