የዮሐንስ ወንጌል 4:7-30

የዮሐንስ ወንጌል 4:7-30 አማ05

በዚያን ጊዜ አንዲት የሰማርያ አገር ሴት ውሃ ልትቀዳ ወደ ጒድጓዱ መጣች፤ ኢየሱስም “ውሃ አጠጪኝ!” አላት። በዚያን ወቅት ደቀ መዛሙርቱ ምግብ ሊገዙ ወደ ከተማ ሄደው ነበር። ይህችም ሳምራዊት ሴት ኢየሱስን፦ “አንተ ከአይሁድ ወገን ሆነህ እንዴት እኔን ሳምራዊቷን ‘ውሃ አጠጪኝ!’ ብለህ ትጠይቀኛለህ?” አለችው፤ ይህን ማለትዋ፥ አይሁድ ከሳምራውያን ጋር ስምምነት ስላልነበራቸው ነው። ኢየሱስም “የእግዚአብሔርን ስጦታና ‘ውሃ አጠጪኝ!’ የሚልሽ ማን እንደ ሆነ ብታውቂው ኖሮ፥ እርሱን መለመን የሚገባሽ አንቺ ነበርሽ፤ እርሱም የሕይወትን ውሃ ይሰጥሽ ነበር” አላት። እርስዋም እንዲህ ስትል መለሰች፤ “ጌታ ሆይ! አንተ መቅጃ የለህም፤ ጒድጓዱም ጥልቅ ነው፤ ታዲያ፥ የሕይወት ውሃ ከየት ታገኛለህ? አንተ ይህን ጒድጓድ ከሰጠን ከአባታችን ከያዕቆብ ትበልጣለህን? እርሱና ልጆቹ፥ ከብቶቹም ከዚህ ጒድጓድ ጠጥተዋል።” ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰላት፤ “ከዚህ ውሃ የሚጠጣ ሁሉ እንደገና ይጠማዋል፤ እኔ ከምሰጠው ውሃ የሚጠጣ ለዘለዓለም ከቶ አይጠማም፤ እኔ የምሰጠው ውሃ፥ ለሚጠጣው ሰው ለዘለዓለም ሕይወት የሚፈልቅ የውሃ ምንጭ ይሆናል።” ሴትዮዋም “ጌታ ሆይ! ከእንግዲህ ወዲህ ውሃ እንዳይጠማኝና ወደዚህም ለመቅዳት እንዳልመጣ እባክህ እንዲህ ዐይነቱን ውሃ ስጠኝ!” አለችው። ኢየሱስም “ሂጂና ባልሽን ጠርተሽ ተመለሺ” አላት። ሴትዮዋም “ባል የለኝም” ስትል መለሰች፤ በዚህ ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አላት፦ “ባል የለኝም ማለትሽ ልክ ነው፤ አምስት ባሎች ነበሩሽ፤ አሁንም ከአንቺ ጋር ያለው ሰው ባልሽ አይደለም፤ ስለዚህ እውነቱን ተናግረሻል።” ሴትዮዋም እንዲህ አለችው፤ “ጌታ ሆይ! አንተ ነቢይ እንደ ሆንክ አሁን ዐወቅሁ፤ አባቶቻችን በዚህ ተራራ ላይ ሰገዱ፤ እናንተ ግን ‘ሰዎች ሊሰግዱ የሚገባቸው በኢየሩሳሌም ነው’ ትላላችሁ።” ኢየሱስም እንዲህ አላት፦ “አንቺ ሴት፥ በዚህ ተራራ ላይ ወይም በኢየሩሳሌም ለአብ የማትሰግዱበት ጊዜ እንደሚመጣ እመኚኝ፤ እናንተ ለማታውቁት አምላክ ትሰግዳላችሁ፤ እኛ ግን መዳን የሚመጣው ከአይሁድ ስለ ሆነ ለምናውቀው አምላክ እንሰግዳለን። ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ፥ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል፤ እንዲያውም አሁን መጥቶአል፤ አብም የሚፈልገው በዚህ መንገድ የሚሰግዱለትን ነው። እግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ይገባቸዋል።” ሴትዮዋም “ክርስቶስ የሚባል መሲሕ እንደሚመጣ ዐውቃለሁ፤ እርሱ ሲመጣ ሁሉን ነገር ይነግረናል” አለችው። ኢየሱስም “እነሆ! አሁን የማነጋግርሽ እኔ እርሱ ነኝ” አላት። በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ከሄዱበት ተመልሰው መጡ፤ ኢየሱስ ከሴት ጋር በመነጋገሩ ተገረሙ፤ ይሁን እንጂ “ምን ትፈልጋለህ? ወይም ከእርስዋ ጋር ለምን ትነጋገራለህ?” ብሎ የጠየቀው ማንም አልነበረም። ከዚህ በኋላ ሴትዮዋ እንስራዋን ትታ ወደ ከተማ ሄደችና ለሰዎቹ እንዲህ አለች፦ “የሠራሁትን ሁሉ የነገረኝን ሰው ኑ እዩ! ምናልባት እርሱ መሲሕ ይሆንን?” ሰዎቹም ከከተማ ወጥተው ወደ ኢየሱስ ሄዱ።