በዚያው በሳምንቱ በመጀመሪያው ቀን እሑድ ማታ ደቀ መዛሙርቱ የአይሁድን ባለሥልጣኖች በመፍራት፥ በራፎቹን ዘግተው፥ በቤት ውስጥ ተሰብስበው ነበር፤ በሮቹ ተዘግተው ሳለ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ተሰበሰቡበት ቤት ገባ፤ በመካከላቸውም ቆሞ፥ “ሰላም ለእናንተ ይሁን!” አላቸው። ይህንንም ብሎ እጆቹንና ጐኑን አሳያቸው፤ ደቀ መዛሙርቱም ጌታን ባዩ ጊዜ ደስ አላቸው። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ እንደገና “ሰላም ለእናንተ ይሁን! አብ እኔን እንደ ላከኝ እኔም እናንተን እልካችኋለሁ” አላቸው። ይህን ብሎ እፍ አለባቸውና “መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ፤ እናንተ የሰዎችን ኃጢአት ይቅር ብትሉ ይቅር ይባልላቸዋል፤ እናንተ የሰዎችን ኃጢአት ይቅር ባትሉ ግን፥ ይቅር አይባልላቸውም” አላቸው። ኢየሱስ ወደ ደቀ መዛሙርቱ በመጣ ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ፥ ዲዲሞስ የተባለው ቶማስ ከእነርሱ ጋር አልነበረም። ስለዚህ ሌሎች ደቀ መዛሙርት ቶማስን “ጌታን አየነው” አሉት። እርሱ ግን “በምስማር የተወጉትን እጆቹን ካላየሁና ጣቴን በምስማር በተወጋው ውስጥ ካላገባሁ፥ እጄንም በጐኑ ቊስል ካላገባሁ አላምንም” አላቸው። ከስምንት ቀን በኋላ ደቀ መዛሙርቱ እንደገና በቤት ውስጥ ነበሩ፤ ቶማስም አብሮአቸው ነበር፤ በሮቹ ተዘግተው ሳሉ ኢየሱስ መጥቶ በመካከላቸው ቆመና “ሰላም ለእናንተ ይሁን!” አላቸው። ከዚህ በኋላ ቶማስን፥ “ጣትህን ወዲህ አምጣና እጆቼን እይ፤ እጅህንም አምጣና በጐኔ ውስጥ አግባው፤ እመን እንጂ እምነተ ቢስ አትሁን” አለው። ቶማስም “ጌታዬ! አምላኬም!” ሲል መለሰለት። ኢየሱስም ቶማስን፥ “አንተስ ስለ አየኸኝ አመንክ፤ ሳያዩኝ የሚያምኑ ግን የተመሰገኑ ናቸው” አለው።
የዮሐንስ ወንጌል 20 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የዮሐንስ ወንጌል 20:19-29
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች