የዮሐንስ ወንጌል 19:4-14

የዮሐንስ ወንጌል 19:4-14 አማ05

ጲላጦስ እንደገና ወደ ውጪ ወጥቶ “እነሆ ምንም በደል እንዳላገኘሁበት እንድታውቁ እርሱን ወደ ውጪ አወጣላችኋለሁ” አላቸው፤ ስለዚህ ኢየሱስ የእሾኽ አክሊል ደፍቶና ቀይ ልብስ ለብሶ ወደ ውጪ ወጣ፤ ጲላጦስም “እነሆ፥ ሰውየው!” አላቸው። የካህናት አለቆችና የዘብ ኀላፊዎች ኢየሱስን ባዩት ጊዜ “ስቀለው! ስቀለው!” እያሉ ጮኹ። ጲላጦስ ግን “እኔ በበኩሌ ምንም በደል አላገኘሁበትም፤ ብትፈልጉ እናንተ ወስዳችሁ ስቀሉት” አላቸው። አይሁድም “እኛ ሕግ አለን፤ ይህ ሰው ራሱን የእግዚአብሔር ልጅ ስላደረገ በሕጋችን መሠረት መሞት ይገባዋል” አሉ። ይህን ሁሉ ነገር በሰማ ጊዜ ጲላጦስ በይበልጥ ፈራ፤ ወደ ግቢው ገባና ኢየሱስን “አንተ ከየት ነህ?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስ ግን ምንም አልመለሰለትም። ስለዚህ ጲላጦስ “አትነግረኝምን? እኔ ልፈታህ ወይም ልሰቅልህ ሥልጣን እንዳለኝ አታውቅምን?” አለው፤ ኢየሱስም “ከእግዚአብሔር ሥልጣን ባይሰጥህ ኖሮ በእኔ ላይ ምንም ሥልጣን ባልኖረህ ነበር፤ ሆኖም ለአንተ አሳልፎ የሰጠኝ የባሰ ኃጢአት አለበት” አለው። ጲላጦስ ይህን የኢየሱስን አነጋገር በሰማ ጊዜ ፈቶ ሊለቀው ፈልጎ ነበር፤ አይሁድ ግን “ይህን ሰው ከፈታኸው አንተ የሮም ንጉሠ ነገሥት ወዳጅ አይደለህም፤ ራሱን ንጉሥ የሚያደርግ ሁሉ የንጉሠ ነገሥቱ ጠላት ነው!” እያሉ ጮኹ። ጲላጦስ ይህን በሰማ ጊዜ ኢየሱስን ወደ ውጪ አውጥቶ “ጠፍጣፋ ድንጋይ” በተባለው ስፍራ በፍርድ ወንበር ተቀመጠ፤ ይህ ስፍራ በዕብራይስጥ ቋንቋ “ገበታ” ይባላል። የፋሲካ በዓል የዝግጅት ቀን ነበረ፤ ጊዜውም ወደ ስድስት ሰዓት ገደማ ነበረ፤ በዚያን ጊዜ ጲላጦስ አይሁድን “እነሆ ንጉሣችሁ!” አላቸው።