ጲላጦስ “የናዝሬቱ ኢየሱስ፥ የአይሁድ ንጉሥ” የሚል ጽሑፍ ጽፎ በመስቀሉ ራስጌ ላይ አኖረው። ኢየሱስ የተሰቀለበት ስፍራ ለከተማ ቅርብ ስለ ነበር፥ ከአይሁድ ብዙዎቹ ጽሑፉን አነበቡት፤ ጽሑፉም የተጻፈው በዕብራይስጥ፥ በላቲንና በግሪክ ቋንቋ ነበር። የአይሁድ ካህናት አለቆች ጲላጦስን፥ “አንተ ‘የአይሁድ ንጉሥ’ ብለህ አትጻፍ፤ ነገር ግን ‘ይህ ሰው እኔ የአይሁድ ንጉሥ ነኝ’ ብሎአል ብለህ ጻፍ” አሉት። ጲላጦስ ግን “የጻፍኩትን ጽፌአለሁ” ሲል መለሰ። ወታደሮቹ ኢየሱስን ከሰቀሉት በኋላ፥ ልብሶቹን ወስደው፥ ለእያንዳንዱ ወታደር አንድ ክፍል እንዲደርስ በአራት ከፋፈሉአቸው፤ እጀ ጠባቡንም እንዲሁ አደረጉ፤ ነገር ግን እጀ ጠባቡ ሳይሰፋ፥ ከላይ እስከ ታች ወጥ ሆኖ የተሠራ ነበር፤ ስለዚህ ወታደሮቹ “ለማን እንደሚደርስ ለማወቅ ዕጣ እንጣጣልበት እንጂ፥ አንቅደደው” ተባባሉ። ይህም የሆነው፥ “ልብሴን ተከፋፈሉ፤ በእጀ ጠባቤም ዕጣ ተጣጣሉ” የሚለው የቅዱስ መጽሐፍ ቃል እንዲፈጸም ነው፤ ወታደሮቹም እንዲሁ አደረጉ። በኢየሱስ መስቀል አጠገብ እናቱና የእናቱ እኅት፥ የቀልዮጳ ሚስት ማርያምና መግደላዊት ማርያም ቆመው ነበር፤ ኢየሱስ እናቱንና የሚወደውን ደቀ መዝሙር አጠገቡ ቆመው ባያቸው ጊዜ፥ እናቱን “እናቴ ሆይ! እነሆ፥ ልጅሽ!” አላት። ከዚህ በኋላ ደቀ መዝሙሩን “እነኋት እናትህ!” አለው፤ ከዚያ ሰዓት ጀምሮ ደቀ መዝሙሩ ወደ ቤቱ ወሰዳት። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ አሁን ሁሉም ነገር እንደ ተፈጸመ ዐውቆ በቅዱስ መጽሐፍ የተጻፈውም ቃል እንዲፈጸም “ተጠማሁ!” አለ። እዚያ ሆምጣጤ የሞላበት ዕቃ ተቀምጦ ነበር፤ ስለዚህ እዚያ የነበሩ ሰዎች፥ ሆምጣጤውን በሰፍነግ ሞሉና በሂሶጵ እንጨት አንጠልጥለው ወደ አፉ አቀረቡለት፤ ኢየሱስም ሆምጣጤውን ከቀመሰ በኋላ “ተፈጸመ!” አለ። ራሱን ዘንበል አድርጎም ነፍሱን ሰጠ። ከዚህ በኋላ የአይሁድ ባለሥልጣኖች፥ የተሰቀሉትን ሰዎች ጭን ሰብረው፥ አስከሬናቸውን ከመስቀል እንዲያወርዱአቸው ጲላጦስን ለመኑት፤ ይህንንም ያደረጉበት ምክንያት የሰንበት ዝግጅት ቀን ስለ ነበረና ያ ሰንበትም ትልቅ በዓል ስለ ሆነ፥ በሰንበት ቀን ሥጋቸው በመስቀል ላይ እንዳይሆን ነበር። ስለዚህ ወታደሮቹ ሄደው፥ ከኢየሱስ ጋር የተሰቀሉትን ሰዎች ጭን ሰበሩ፤ ወደ ኢየሱስ በሄዱ ጊዜ ግን፥ እርሱ ቀደም ብሎ እንደ ሞተ አይተው፥ ጭኑን አልሰበሩም። ነገር ግን ከወታደሮቹ አንዱ፥ ጐኑን በጦር ወጋው፤ ወዲያውኑ ከጐኑ ደምና ውሃ ወጣ። ይህን ያየ፥ እናንተ እንድታምኑ መሰከረ፤ ምስክርነቱም እውነት ነው፤ የሚናገረውም እውነት እንደ ሆነ፥ እርሱ ያውቃል። ይህም የሆነው፥ “ከእርሱ አንድ አጥንት እንኳ አይሰበርም” የሚለው የቅዱስ መጽሐፍ ቃል እንዲፈጸም ነው። ደግሞም በሌላው የቅዱስ መጽሐፍ ክፍል “ያንን የወጉትን ያዩታል” ይላል። የአይሁድ ባለሥልጣኖችን በመፍራት በስውር የኢየሱስ ደቀ መዝሙር የነበረው የአርማትያሱ ዮሴፍ የኢየሱስን አስከሬን ለመውሰድ ጲላጦስን ለመነ። ጲላጦስም ፈቀደለት። ስለዚህ ዮሴፍ ሄዶ አስከሬኑን ወሰደ። ከዚህ በፊት በሌሊት ወደ ኢየሱስ ሄዶ የነበረው ኒቆዲሞስም አንድ መቶ ነጥርየሚያኽል የከርቤና የሬት ቅልቅል ይዞ መጣ። ሁለቱ ሰዎች የኢየሱስን አስከሬን ወስደው እንደ አይሁድ አገናነዝ ልማድ ከሽቶ ጋር በቀጭን ልብስ ከፈኑት። ኢየሱስ ተሰቅሎ በነበረበት ቦታ አንድ የአትክልት ስፍራ ነበረ፤ በዚያም የአትክልት ስፍራ ውስጥ ማንም ያልተቀበረበት አዲስ መቃብር ነበር። የሰንበት ዝግጅት ቀን ስለ ነበረና መቃብሩም ቅርብ ስለ ነበረ የኢየሱስን አስከሬን እዚያ ቀበሩት።
የዮሐንስ ወንጌል 19 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የዮሐንስ ወንጌል 19:19-42
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች