ኢየሱስ ይህን ካለ በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ቄድሮን ሸለቆ ማዶ ሄደ፤ እዚያ ወደነበረውም የአትክልት ቦታ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ገባ። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ እዚያ ቦታ ዘወትር ይሰበሰቡ ስለ ነበር አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ ያን ቦታ ያውቅ ነበር። ስለዚህ ይሁዳ አንድ የወታደሮች ጭፍራ፥ እንዲሁም ከካህናት አለቆችና ከፈሪሳውያን የተላኩትን የዘብ ኀላፊዎችን አስከትሎ ወደዚያ ቦታ መጣ፤ እነርሱም ፋኖስና ችቦ፥ የጦር መሣሪያም ይዘው ነበር። ኢየሱስም የሚደርስበትን ሁሉ ዐውቆ ወደ እነርሱ ወጣ ብሎ “ማንን ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። እነርሱም “የናዝሬቱን ኢየሱስ እንፈልጋለን” አሉት። እርሱም “እኔ ነኝ!” አላቸው። አሳልፎ የሰጠው ይሁዳም ከእነርሱ ጋር ቆሞ ነበር። ኢየሱስ “እኔ ነኝ” ባላቸው ጊዜ ወደ ኋላ አፈገፈጉና በምድር ላይ ወደቁ። ኢየሱስም “ማንን ትፈልጋላችሁ?” ሲል እንደገና ጠየቃቸው። እነርሱም “የናዝሬቱን ኢየሱስ እንፈልጋለን” አሉ። እርሱም “እኔ ነኝ ብዬአችኋለሁ፤ እንግዲህ የምትፈልጉት እኔን ከሆነ እነዚህን ተዉአቸው፤ ይሂዱ” አለ። ይህም የሆነው፥ “አባት ሆይ፥ ከሰጠኸኝ ሰዎች አንዱን እንኳ አላጠፋሁም” ያለው ቃል እንዲፈጸም ነው። ስምዖን ጴጥሮስ ሰይፍ ይዞ ስለ ነበረ መዘዘና የካህናት አለቃውን አገልጋይ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቈረጠ፤ የአገልጋዩም ስም “ማልኮስ” ይባል ነበር። ኢየሱስ ግን ጴጥሮስን፥ “ሰይፍህን ወደ አፎቱ ክተተው፤ አብ የሰጠኝን የመከራ ጽዋ የማልጠጣው ይመስልሃልን?” አለው። ከዚህ በኋላ ወታደሮቹና አዛዣቸው፥ የአይሁድ የዘብ ኀላፊዎችም ኢየሱስን ይዘው አሰሩት። በመጀመሪያ ወደ ሐና ወሰዱት፤ ሐና በዚያ ዓመት የካህናት አለቃ ለነበረው ለቀያፋ ዐማቱ ነበር። ቀያፋ “አንድ ሰው ስለ ሕዝቡ ቢሞት የተሻለ ነው” ሲል የአይሁድ ባለሥልጣኖችን የመከረ ነው።
የዮሐንስ ወንጌል 18 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የዮሐንስ ወንጌል 18:1-14
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች