የዮሐንስ ወንጌል 16:16-22

የዮሐንስ ወንጌል 16:16-22 አማ05

“ከጥቂት ጊዜ በኋላ አታዩኝም፤ እንደገናም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ታዩኛላችሁ።” ከደቀ መዛሙርቱ አንዳንዶች፥ “ይህ፥ ‘ከጥቂት ጊዜ በኋላ አታዩኝም፤ ደግሞ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ታዩኛላችሁ፤ ደግሞ ወደ አብ እሄዳለሁ’ የሚለን ነገር ምንድን ነው?” ተባባሉ። “እንግዲህ ይህ ‘ከጥቂት ጊዜ በኋላ’ የሚለው ነገር ምንድን ነው? የሚናገረውን ነገር አናውቅም” በመባባል መላልሰው ተጠያየቁ። ኢየሱስም ሊጠይቁት እንደ ፈለጉ ዐውቆ እንዲህ አላቸው፦ “እርስ በርሳችሁ የምትጠያየቁ፥ ‘ከጥቂት ጊዜ በኋላ አታዩኝም፤ ደግሞም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ታዩኛላችሁ’ ስላልኳችሁ ነውን? እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ እናንተ ታለቅሳላችሁ፤ ትጮኻላችሁም፤ ዓለም ግን ደስ ይለዋል፤ እናንተ ታዝናላችሁ፤ ነገር ግን ሐዘናችሁ ወደ ደስታ ይለወጣል። ሴት በምትወልድበት ጊዜ የምጥ ቀንዋ ስለ ደረሰ ታዝናለች፤ ከወለደች በኋላ ግን በዓለም ላይ ሕፃን ስለ ተወለደ ከመደሰትዋ የተነሣ ጭንቀትዋን አታስታውሰውም። እንዲሁም እናንተ አሁን ታዝናላችሁ፤ ነገር ግን እኔ እንደገና አያችኋለሁ፤ ልባችሁም ደስ ይለዋል፤ ደስታችሁንም የሚወስድባችሁ የለም።