ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ ወደ በጎች በረት በበር ሳይሆን በሌላ በኩል የሚገባ ሰው ሌባና ወንበዴ ነው። በበሩ የሚገባ ግን የበጎች እረኛ ነው። ለእርሱ የበር ጠባቂው በሩን ይከፍትለታል፤ በጎቹ ድምፁን ይሰማሉ፤ እርሱም የራሱን በጎች በየስማቸው ይጠራቸዋል፤ እየመራም ወደ ውጪ ያወጣቸዋል። የራሱን በጎች ካስወጣ በኋላም እፊት እፊታቸው ይሄዳል፤ በጎቹም ድምፁን ስለሚያውቁ ይከተሉታል። የሌላውን ድምፅ ግን ስለማያውቁ ከእርሱ ይሸሻሉ እንጂ አይከተሉም።” ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤ እነርሱ ግን የተናገረውን አላስተዋሉም። ስለዚህ ኢየሱስ እንደገና እንዲህ አላቸው፦ “እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ እኔ የበጎች በር ነኝ፤ ከእኔ በፊት የመጡት ሁሉ ሌቦችና ወንበዴዎች ናቸው፤ በጎቹ ግን አልሰሙአቸውም። በሩ እኔ ነኝ፤ በእኔ በኩል የሚገባ ይድናል፤ ይገባል፤ ይወጣል፤ መሰማሪያም ያገኛል። ሌባው የሚመጣው ለመስረቅ፥ ለማረድና ለማጥፋት ብቻ ነው፤ እኔ ግን የመጣሁት ሕይወት እንዲያገኙና የተትረፈረፈ ሕይወት እንዲኖራቸው ነው። “መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ መልካም እረኛ ሕይወቱን ስለ በጎቹ አሳልፎ ይሰጣል። በጎቹ የራሱ ያልሆኑ ቅጥረኛ እንጂ እውነተኛ ያልሆነ እረኛ ግን ተኲላ ሲመጣ በሚያይበት ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፤ ተኲላውም በጎቹን ነጥቆ ይበታትናቸዋል። እረኛው የሚሸሸውም ቅጥረኛ ስለ ሆነና ለበጎቹም ስለማያስብ ነው። መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ እኔ በጎቼን ዐውቃለሁ፤ በጎቼም እኔን ያውቁኛል። እኔ እነርሱን የማውቃቸው አብ እኔን እንደሚያውቀኝና እኔም አብን እንደማውቀው ዐይነት ነው፤ እኔ ስለ በጎቼ ሕይወቴን አሳልፌ እሰጣለሁ። በዚህ መንጋ ውስጥ ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱንም ማምጣት ይገባኛል፤ እነርሱ ድምፄን ይሰማሉ፤ አንድ መንጋም ይሆናሉ፤ እረኛውም አንድ ይሆናል። “እንደገና መልሼ እወስዳት ዘንድ ሕይወቴን የምሰጥ ስለ ሆንኩ አብ እኔን ይወደኛል።
የዮሐንስ ወንጌል 10 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የዮሐንስ ወንጌል 10:1-17
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች