የዮሐንስ ወንጌል 1:43-51

የዮሐንስ ወንጌል 1:43-51 አማ05

በማግስቱ ኢየሱስ ወደ ገሊላ ለመሄድ ፈለገ፤ ፊልጶስንም አገኘውና “ተከተለኝ!” አለው። ፊልጶስ እንደ እንድርያስና እንደ ጴጥሮስ የቤተ ሳይዳ ከተማ ሰው ነበረ። ፊልጶስ ናትናኤልን አግኝቶ፥ “ሙሴ በሕግ መጽሐፍ፥ ነቢያትም በትንቢት መጻሕፍት ስለ እርሱ የጻፉለትን አገኘነው፤ እርሱም የዮሴፍ ልጅ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነው” አለው። ናትናኤል ግን፥ “ከናዝሬት መልካም ነገር ከቶ ሊገኝ ይችላልን?” አለው። ፊልጶስም “መጥተህ እይ!” አለው። ናትናኤል ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ ኢየሱስ “እነሆ! ተንኰል የሌለበት እውነተኛ የእስራኤል ሰው!” ሲል ስለ እርሱ ተናገረ። ናትናኤልም “የት ታውቀኛለህ?” አለው። ኢየሱስም “ፊልጶስ ሳይጠራህ በፊት ከበለስ ዛፍ ሥር ሆነህ አይቼሃለሁ” ሲል መለሰለት። በዚህ ጊዜ ናትናኤል፥ “መምህር ሆይ! አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ! አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ!” አለ። ኢየሱስም እንዲህ አለ፦ “አንተ ያመንከው፥ ‘ከበለስ ዛፍ ሥር ሆነህ አይቼሃለሁ’ ስላልኩህ ነውን? ከዚህ የበለጡ ነገሮችን ገና ታያለህ። እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፦ ሰማይ ሲከፈት የእግዚአብሔር መላእክትም በሰው ልጅ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ታያላችሁ።”