የዮሐንስ ወንጌል 1:19-28

የዮሐንስ ወንጌል 1:19-28 አማ05

የአይሁድ ባለሥልጣኖች ከኢየሩሳሌም ካህናትንና ሌዋውያንን ወደ ዮሐንስ ልከው፦ “አንተ ማን ነህ?” ብለው ባስጠየቁት ጊዜ የሰጠው ምስክርነት የሚከተለው ነው፤ እርሱ “እኔ መሲሕ አይደለሁም” ሲል መሰከረ እንጂ አልካደም። እነርሱም “ታዲያ አንተ ማን ነህ? ኤልያስ ነህን?” ሲሉ ጠየቁት። እርሱም “አይደለሁም” ሲል መለሰላቸው። እነርሱም “ይመጣል የተባለው ነቢይ ነህን?” አሉት። እርሱም “አይደለሁም” አለ። እነርሱም “ታዲያ አንተ ማን ነህ? ለላኩን ሰዎች መልሱን እንድንነግር ስለ ራስህ ምን ትላለህ?” አሉት። እርሱም “ነቢዩ ኢሳይያስ እንደ ተናገረው እኔ ‘የጌታን መንገድ አቅኑ’ እያለ በበረሓ የሚጮኽ ሰው ድምፅ ነኝ” አለ። ሰዎቹ የተላኩት ከፈሪሳውያን ነበረ፤ ስለዚህ “አንተ መሲሕ ወይም ኤልያስ ወይም ይመጣል የተባለው ነቢይ ካልሆንክ ታዲያ፥ ስለምን ታጠምቃለህ?” ሲሉ ጠየቁት። ዮሐንስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እኔ የማጠምቀው በውሃ ነው፤ ነገር ግን እናንተ የማታውቁት በመካከላችሁ ቆሞአል። እርሱ ከእኔ በኋላ የሚመጣ ነው፤ እኔ የጫማውን ማሰሪያ ለመፍታት እንኳ የበቃሁ አይደለሁም።” ይህ የሆነው ዮሐንስ ያጠምቅ በነበረበት ከዮርዳኖስ ወንዝ ማዶ በምትገኘው በቢታንያ ከተማ ነው።