ትንቢተ ኤርምያስ 8
8
1“በዚያን ጊዜ የይሁዳ ነገሥታትና የመኳንንት ዐፅሞች እንዲሁም የካህናቱና የነቢያቱ የሌላውም የኢየሩሳሌም ነዋሪ ሕዝብ ዐፅሞች ሁሉ ከየመቃብሩ ተለቅመው ይወጣሉ። 2ዐፅሞቻቸው ተሰብስበው በመቀበር ፈንታ፥ እንደ ጒድፍ የትም ይጣላሉ፤ እነርሱም፥ ሕዝቡ በማምለክና ምክር በመጠየቅ በፍቅር ያገለግሉአቸው በነበሩት በፀሐይ፥ በጨረቃና በከዋክብት ፊት ይበተናሉ። 3ከዚህም ክፉ ትውልድ የተረፉትና እኔ በበተንኳቸው ቦታ የሚኖሩትም ሕዝብ ከመኖር ይልቅ መሞትን ይመርጣሉ።”
ኃጢአት ያስከተለው ቅጣት
4እግዚአብሔር ለሕዝቡ እንዲህ ብለህ ተናገር አለኝ፦ “የወደቀ ሰው እንደገና መነሣት አይችልምን? መንገድ ተሳስቶት የጠፋ ሰው አይመለስምን? 5ታዲያ ሕዝቤ ወደ እኔ በመመለስ ፈንታ እንደ ራቃችሁ የምትቀሩት ስለምንድነው? ወደ እኔ መመለስን እምቢ ብላችሁ ወደ ጣዖት አዘነበላችሁ። 6እኔ በጥንቃቄ አዳመጥኩ፤ እናንተ ግን እውነት አልተናገራችሁም፤ ከእናንተ መካከል ስለ ክፉ ሥራው የተጸጸተ አንድም የለም፤ ‘የፈጸምኩት በደል ምንድን ነው?’ ብሎ የጠየቀም የለም፤ እያንዳንዳችሁም ወደ ጦርነት እንደሚሮጥ ፈረስ በየፊናችሁ ትሮጣላችሁ። 7ሽመላዎች እንኳ የሚመለሱበትን ጊዜ ያውቃሉ፤ ዋኖሶች፥ ጨረባዎች፥ ዋርዳዎችም በኅብረት የሚሰደዱበትን ጊዜ ያውቃሉ፤ እናንተ ሕዝቤ ግን እንድትተዳደሩበት የሰጠኋችሁን ሕግ አታውቁም። 8ታዲያ ‘እኛ ጠቢባን ነን፤ የእግዚአብሔርንም ሕግ እናውቃለን’ የምትሉት ስለምንድን ነው? ሐሰተኞች ጸሐፊዎች ሕጌን እንዳዛቡ አትመለከቱምን? 9ጥበበኞቻችሁ ኀፍረት ደርሶባቸዋል፤ በወጥመድ ተይዘውም ግራ ገብቶአቸዋል፤ እነርሱ ቃሌን ትተዋል፤ ታዲያ ምን ዐይነት ጥበብ ሊኖራቸው ይችላል? 10ስለዚህ እርሻቸውን ሁሉ ለሌሎች ርስት አድርጌ እሰጣለሁ፤ ሚስቶቻቸውንም ሌሎች ወንዶች እንዲቀሙአቸው አደርጋለሁ፤ ታላላቆችም ሆኑ ታናናሾች እያንዳንዱ ሰው በማታለል ጥቅምን ያግበሰብሳል፤ ነቢያትና ካህናት ሳይቀሩ ሕዝቡን ያታልላሉ፤ 11የሕዝቤንም የስብራት ቊስል እንደ ቡጭራት በመቊጠር በሚገባ አያክሙትም፤ እንዲሁም ሰላም ሳይኖር ‘ሰላም ነው ሰላም ነው’ ይላሉ። #ሕዝ. 13፥10። 12ሕዝቤ ሆይ! ይህን ሁሉ አጸያፊ ነገር ስታደርጉ ጥቂት ኀፍረት ተሰምቶአችሁ ነበርን? ኀፍረት ሊሰማችሁ ቀርቶ ዐይናችሁ እንኳ ሰበር አላለም፤ ስለዚህ ሌሎች እንደ ወደቁ እናንተም ትወድቃላችሁ፤ እኔ በምቀጣችሁ ጊዜ ፍጻሜአችሁ ይሆናል፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ። #ኤር. 6፥12-15።
13“ገበሬ ሰብሉን እንደሚሰበስብ ሕዝቤን ልሰበስብ ፈለግኹ፤ እነርሱ ግን ዘለላ እንደሌለው የወይን ተክል ፍሬ አልባ እንደ ሆነ የበለስ ዛፍና ቅጠሉ እንደ ረገፈ ተክል ሆኑብኝ፤ በዚህ ምክንያት የሰጠኋቸውን ምድር ባዕዳን እንዲወስዱባቸው አደረግሁ።”
14የእግዚአብሔር ሕዝብ እንዲህ ይላሉ፦ “ዝም ብለን መቀመጣችን ለምንድን ነው? አምላካችን እግዚአብሔር ሞት ፈርዶብናል፤ እርሱን ስለ በደልን የተመረዘ ውሃ እንድንጠጣ አድርጎናል። ኑ! ወደተመሸጉ ከተሞች ሮጠን እዚያ እንሙት፤ 15ሰላምና ፈውስ የምናገኝበት ጊዜ ይመጣልናል ብለን ተስፋ አድርገን ነበር፤ በዚህ ፈንታ ሽብር በመምጣቱ ምኞታችን ከንቱ ሆኖ ቀረ። 16ጠላቶቻችን እስከ ዳን ከተማ ደርሰዋል፤ ፈረሶቻቸው ሲያንኮራፉ ድምፃቸው ይሰማል፤ ሰንጋ ፈረሶቻቸውም ሲያሽካኩ ምድር ትናወጣለች፤ ጠላቶቻችን የመጡት ምንም ሳያስቀሩ ሕዝባችንንና ከተሞቻችንን እንዲሁም በውስጡ ያለውን ነገር ሁሉ ለማጥፋት ነው።”
17እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ተጠንቀቁ! እነሆ የአስማተኛ ድግምት ሊገታቸው የማይችል መርዘኛ እባቦችንና እፉኝቶችን በመካከላችሁ እልካለሁ፤ እነርሱም ይነድፉአችኋል።”
ኤርምያስ ስለ ሕዝቡ ማዘኑ
18መጽናናት የማይገኝለት ብርቱ ሐዘን ደርሶብኛል፤
ልቤም እጅግ ዝሎአል።
19እስቲ አድምጡ! “እግዚአብሔር ዳግመኛ በጽዮን አይገኝምን?
የጽዮን ንጉሥ ዳግመኛ በዚያ አይኖርምን?”
እያሉ ሕዝቤ በምድሪቱ ሁሉ ላይ ሲጮኹ እሰማለሁ።
ንጉሣቸው እግዚአብሔርም፦
“ጣዖቶቻችሁን በማምለክና ለባዕድ አማልክታችሁም በመስገድ
የምታስቈጡኝ ስለምንድን ነው?” ሲል ይመልስላቸዋል፤
20ሕዝቡም “እነሆ የመከር ወራት አለፈ፤ በጋውም ተፈጸመ፤
እኛ ግን አልዳንም!” በማለት ይጮኻሉ።
21ሕዝቤ በመሰበሩ የእኔም ልብ ተሰብሮአል፤
ፍርሀትም ይዞኝ አለቅሳለሁ።
22በገለዓድ የቅባት መድኃኒት የለምን?
ሐኪሞችስ በዚያ አይገኙምን?
ታዲያ ሕዝቤ የማይፈወሱት ስለምንድን ነው?
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 8: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997