ትንቢተ ኤርምያስ 9
9
1ስለ ተገደሉት ሕዝቤ ቀንና ሌሊት አለቅስ ዘንድ፥
ራሴ የውሃ ጒድጓድ፥
ዐይኖቼም የእንባ ምንጭ በሆኑ እንዴት በወደድሁ ነበር!
2ሕዝቤ እምነተ ቢሶችና አታላዮች ስለ ሆኑ፥
ከእነርሱ ተለይቼ በምድረ በዳ ውስጥ የምኖርበት
የመንገደኞች ማደሪያ ቦታ ባገኝ፥ እንዴት ደስ ባለኝ ነበር!
3እነርሱ በአንደበታቸው ሐሰት ለመናገር ዘወትር የተዘጋጁ ናቸው፤
ስለዚህም በምድሪቱ ላይ በእውነት ፈንታ ሐሰት ነግሦአል።
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“ሕዝቤ ከአንዱ ኃጢአት ወደ ሌላው ኃጢአት ይተላለፋሉ፤
የእኔንም አምላክነት ዐውቀው አላከበሩኝም።”
4እያንዳንዱ ከባልንጀራው ተንኰል ይጠንቀቅ፤
ወንድሙን እንኳ ቢሆን ማመን የለበትም፤
ወንድም የተባለ ሁሉ (እንደ ያዕቆብ) አታላይ ሆኖአል፤
ወዳጅ የተባለም ሁሉ የባልንጀራውን ስም ያጠፋል።
5ሁሉም ባልንጀራውን በማሞኘት ያሳስታል፤
እውነት የሚናገርም የለም፤
አንደበታቸው ውሸት መናገርን እንዲለማመድ አድርገውታል፤
ኃጢአት በመሥራት ሰውነታቸውን ያደክማሉ።
6ግፍን በግፍ ላይ ማታለልንም በማታለል ላይ እየጨመሩ ይሄዳሉ፤
“እኔም አምላካቸው መሆኔን ለመቀበል
እምቢ ብለዋል” ይላል እግዚአብሔር።
7ከዚህም የተነሣ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“ሕዝቤን ለማጥራት እንደ ብረት እፈትናቸዋለሁ፤
ሕዝቤ ክፉ ነገር ስለ ፈጸሙ
ይህን ከማድረግ በቀር ሌላ ምን አደርጋቸዋለሁ?
8አንደበታቸው ዘወትር ተንኰል ስለሚናገር፥
እንደ አደገኛ ፍላጻ ነው፤
እያንዳንዱ ባልንጀራውን በፍቅር ቃል ያነጋግረዋል፤
ነገር ግን በስውር ወጥመድ ይዘረጋበታል።
9ታዲያ በዚህ ሁሉ ነገር እነርሱን ልቀጣቸውና
እንደነዚህ ያሉትንስ ሕዝብ ልበቀላቸው አይገባኝምን?
እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”
10እኔም እንዲህ አልኩ፦
“ሁሉም ወና ስለ ሆኑና በእነርሱም ላይ የሚዘዋወርባቸው ስለሌለ፥
ስለ ተራራዎች አዝናለሁ፤ ስለ ሜዳዎችም አለቅሳለሁ፤
የከብቶች ድምፅ ዳግመኛ አይሰማም፤
የሰማይ ወፎችና የምድር አራዊት ሁሉ ሸሽተው ጠፍተዋል።”
11እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“ኢየሩሳሌምን የፍርስራሽ ክምር አደርጋታለሁ፤
የቀበሮዎችም መፈንጫ ትሆናለች፤
የይሁዳንም ከተሞች ማንም የማይኖርባቸው ባድማ አደርጋቸዋለሁ።”
12እኔም እንዲህ አልኩ፦ “ምድሪቱ ማንም ሊዘዋወርባት የማይችል ደረቅ በረሓና ጠፍ መሆንዋ ስለ ምንድን ነው? ይህንንስ የሚያስተውል ጥበበኛ ሰው ማን ነው? ለሌሎች ማስረዳት ይችል ዘንድ የገለጥክለትስ ማን ነው?”
13እግዚአብሔርም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ይህ ሁሉ ሊሆን የቻለው ሕዝቤ እኔ የሰጠኋቸውን ሕግ በመተዋቸው ነው፤ እነርሱ ለእኔ አልታዘዙም፤ የነገርኳቸውንም ሁሉ አልፈጸሙም። 14ይህን በማድረግ ፈንታ እልኸኞች ሆኑ፤ አባቶቻቸው ባስተማሩአቸውም መሠረት ለባዓል ምስሎች ሰገዱ። 15ስለዚህ የእስራኤል አምላክ እኔ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር የማደርገውን ነገር ልንገራችሁ፤ ይህ ሕዝብ ምግቡ መራራ መጠጡም የተመረዘ ውሃ እንዲሆንበት አደርጋለሁ። 16እነርሱም ሆኑ የቀድሞ አባቶቻቸው በማያውቁአቸው አሕዛብ መካከል እበትናቸዋለሁ፤ እስከማጠፋቸውም ድረስ በሰይፍ አሳድዳቸዋለሁ።”
የኢየሩሳሌም ሕዝብ ርዳታ ለማግኘት የሚያሰሙት ጩኸት
17የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“አሁንም አስቡ፥ አልቃሾችን በአንድነት ሰብስቡ፤
ሙሾ የሚያወጡ ሴቶችንም ጥሩ።”
18ሕዝቡም እንዲህ አሉ፦
“ዐይናችን በእንባ እንዲርስ፥
በጉንጫችንም እንባው እንዲወርድ፥
አስለቃሾች በቶሎ ሙሾ እንዲያወጡ ንገሩአቸው።”
19በጽዮን “ወዮልን ልንጠፋ ነው!
ፈጽሞም ተዋረድን!
ቤቶቻችን ስለ ፈራረሱ አገራችንን ለቀን መሄዳችን ነው”
እየተባለ የሚያስተጋባውን የለቅሶ ጩኸት አድምጡ።
20እኔም እንዲህ አልኩ፦
“እናንተ ሴቶች፥ እግዚአብሔር የሚለውን አድምጡ፤
ቃሉንም ለመቀበል የተዘጋጃችሁ ሁኑ፤
እንዴት ማልቀስ እንደሚገባቸው ሴቶች ልጆቻችሁን አስተምሩ፤
ሙሾ የማውጣትንም ዘዴ ለወዳጆቻችሁ አስጠኑ።
21ሞት በየመስኮቶቻችን ገብቶአል፤
በየቤተ መንግሥታችንም ውስጥ ገብቷል፤
ልጆችን በየመንገዱ፥ ጐልማሶችንም በየአደባባዩ ቀሥፎአል።
22የሰው ሬሳ የትም እንደሚጣል ቈሻሻ በየስፍራው ተበትኖአል፤
አጫጆች ቈርጠው እንደ ጣሉትና ማንም እንደማይሰበስበው ቃርሚያ ሆኖአል፤
እግዚአብሔር እንድናገር ያዘዘኝ ይህ ነው።”
23እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“ጠቢብ በጥበቡ፥
ብርቱ ሰውም በኀይሉ፥
ባለጸጋም በሀብቱ አይመካ፤
24አንድ ሰው መመካት ካለበት
በምድር ላይ ምሕረትን፥
ትክክለኛ ፍርድንና እውነትን የማስገኝ እኔ አምላክ መሆኔን በመረዳት ይመካ፤
እኔም ደስ የሚያሰኘኝ ይኸው ነው፤
እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።” #1ቆሮ. 1፥31፤ 2ቆሮ. 10፥17።
25እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ለስም ብቻ የተገረዙትን ሁሉ የምቀጣበት ጊዜ ይመጣል፤ 26የግብጽ፥ የይሁዳ፥ የኤዶም፥ የአሞን፥ የሞአብና በበረሓ ጠረፍ የሚኖሩ የግንባራቸውን ግራና ቀኝ ጠጒር የተላጩ ሕዝቦች እንዲሁም የእስራኤል ሕዝብ ከልባቸው ያልተገረዙ ስለ ሆኑ ሁሉንም በአንድ ዐይነት እቀጣለሁ።”
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 9: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997