የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኤርምያስ 6

6
የኢየሩሳሌም በጠላት መከበብ
1የብንያም ሕዝብ ሆይ! ሕይወታችሁን ለማትረፍ ሽሹ! ከኢየሩሳሌምም ውጡ! በተቆዓ የጥሩምባ ድምፅ አሰሙ፤ በቤትሀካሬም ለምልክት የሚሆን እሳት አንድዱ! መቅሠፍትና ጥፋት ከሰሜን በኩል ሊመጣ ነው። 2ውብና አስደሳች የሆነችው የጽዮን ከተማ ትጠፋለች። 3እረኞች ከነመንጋቸው እዚያ ይሰፍራሉ፤ ድንኳኖቻቸውን በከተማይቱ ዙሪያ ይተክላሉ፤ እያንዳንዱም ደስ ባለው ስፍራ መንጋውን ያሰማራል። 4ጠላቶችዋም እንዲህ ይላሉ፦ “ኢየሩሳሌምን ለመውጋት እንዘጋጅ! ተነሡ! በእኩለ ቀን ላይ አደጋ እንጣልባት! እንዲያውም ዘግይተናል፤ ቀኑ ሊመሽ ተቃርቦአል፤ ፀሐይም ልትጠልቅ በመቃረብዋ ጥላው እየረዘመ ሄዶአል፤ 5ስለዚህ ተነሡ፥ በሌሊት አደጋ ጥለን የከተማይቱን ምሽጎች እናፈራርስ።”
6ስለዚህም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ዛፎችን ቊረጡ፤ በኢየሩሳሌም ዙሪያ እንደምሽግ ሆኖ የሚያገለግል ዐፈር ቈልሉ፤ እርስዋ በግፍ የተሞላች ስለ ሆነ መቀጣት የሚገባት ከተማ ናት፤ 7ጒድጓድ ውሃን እንደሚያፈልቅ፥ ኢየሩሳሌምም የክፋት ሁሉ መፍለቂያ ናት፤ በእርስዋ የሚሰማው የግፍና የጥፋት ጩኸት ብቻ ነው፤ ዘወትር የሚታይባትም ሕመምና ቊስል ነው። 8እናንተ የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሆይ! ይህ ሁሉ መከራ ማስጠንቀቂያ ይሁናችሁ፤ አለበለዚያ ከፊቴ አስወግዳችኋለሁ፤ ከተማችሁን ወደ ምድረ በዳ ለውጬ ማንም እንዳይኖርባት አደርጋለሁ።”
የእስራኤል ዐመፀኛነት
9የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ከእስራኤል የተረፉትን የወይን ዘለላን እንደሚለቅም ሰው ልቀሙ፤ መላልሳችሁ ወይንን እንደሚለቅም ሰው እጃችሁን በቅርንጫፎቹ ላይ ዘርጉ።”
10እኔም መልሼ እንዲህ አልኩ፦ “እኔ ብነግራቸውና ባስጠነቅቃቸው ማን ሊሰማኝ ይችላል? እነርሱ እልኸኞች ስለ ሆኑ፥ ቃልህን መስማት አይፈልጉም፤ የአንተን ቃል ስነግራቸው በንቀት መሳቂያ ያደርጉኛል። 11ጌታ ሆይ! አንተ በእነርሱ ላይ ያለህ ቊጣ በእኔም ውስጥ ይነዳል። ከቶም ልታገሠው አልችልም።”
እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፦ “ቊጣዬን በመንገድ ላይ በሚገኙ ሕፃናትና በተሰበሰቡ ወጣቶች ላይ አፍስሰው፤ ባልና ሚስት በአንድነት ይወሰዳሉ፤ በዕድሜ ለገፉ ሽማግሌዎች እንኳ ምሕረት አይደረግላቸውም።” 12እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እኔ የዚህችን ምድር ሕዝብ በምቀጣበት ጊዜ ቤቶቻቸው፥ እርሻዎቻቸውና ሚስቶቻቸው ጭምር ለሌሎች ይሰጣሉ። 13ታላላቆችም ሆኑ ታናናሾች እያንዳንዱ ሰው ሕገወጥ በሆነ መንገድ ጥቅሙን ያግበሰብሳል፤ ነቢያትና ካህናት ሳይቀሩ ሕዝቡን ያታልላሉ፤ 14የሕዝቤንም የስብራት ቊስል እንደ ቡጭራት በመቊጠር በሚገባ አያክሙትም፤ እንዲሁም ሰላም ሳይኖር ‘ሰላም ነው፤ ሰላም ነው፤’ ይላሉ። #ሕዝ. 13፥10። 15ይህን ሁሉ አጸያፊ ነገር ሠርተው ኀፍረት ተሰምቶአቸው ነበርን? እንኳንስ ሊያፍሩ ቀርቶ ዐይናቸው እንኳ ሰበር አላለም፤ ስለዚህ ሌሎች እንደ ወደቁ እነርሱም ይወድቃሉ፤ እኔ በምቀጣቸው ጊዜ ፍጻሜአቸው ይሆናል፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።” #ኤር. 8፥10-12።
የእስራኤል ከእግዚአብሔር መንገድ መውጣት
16እግዚአብሔር ለሕዝቡ እንዲህ ይላል፦ “በየጐዳናው ቆማችሁ ተመልከቱ፤ ጥንታዊና መልካም የሆነችው መንገድ የትኛዋ እንደ ሆነች ጠይቃችሁ ተረዱ፤ ባገኛችኋትም ጊዜ በእርስዋ ሂዱ፤ በሰላምም ትኖራላችሁ።” #ማቴ. 11፥29።
ሕዝቡ ግን “በእርስዋ አንሄድም!” አሉ። 17ከዚያን በኋላ እግዚአብሔር የማስጠንቀቂያውን ጥሩምባ ድምፅ የሚያሰሙ ጠባቂዎችን አቆመ፤ እነርሱ ግን “አንሰማም” አሉ።
18ስለዚህም እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ “እናንተ ሕዝቦች ስሙ! በሕዝቤ ላይ የማደርገውንም ሁሉ አስተውሉ። 19ምድር ሆይ! ስሚ! እነርሱ ያስተማርኳቸውን ሥርዓት ስለ ተቃወሙ፤ ለሕጌም ስላልታዘዙ ስለ ክፉ ሐሳባቸው ሁሉ እቀጣቸው ዘንድ በሕዝቡ ላይ ጥፋትን አመጣለሁ። 20ከሳባ የሚያመጡልኝ ዕጣን፥ ከሩቅ አገሮች የሚያመጡልኝ ቅመማቅመም ሁሉ ለእኔ ምን ይረባኛል? መባቸውን አልቀበለውም፤ መሥዋዕታቸውም ደስ አያሰኘኝም። 21ስለዚህ ይህ ሕዝብ ተሰናክሎ እንዲወድቅ አደርጋለሁ፤ አባቶችና ልጆች፥ ጓደኛሞችና ጐረቤቶች በአንድነት ይሞታሉ።”
ከሰሜን በኩል የሚቃጣ ወረራ
22እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በሰሜን በኩል ከሚገኝ አገር ወራሪ ይመጣል፤ በሩቅ ያለ ታላቅ ሕዝብም ለጦርነት ተዘጋጅቶአል፤ 23ቀስታቸውንና ሰይፋቸውን አንሥተዋል፤ እነርሱም ምሕረት የሌላቸው ጨካኞች ናቸው፤ ተቀምጠው የሚጋልቡአቸው ፈረሶች፥ የኮቴአቸው ድምፅ እንደ ባሕር ሞገድ ነው። እነሆ እነርሱ ኢየሩሳሌምን ለመውጋት ተዘጋጅተዋል።”
24የኢየሩሳሌም ሕዝብ እንዲህ ይላሉ፦ “ወሬውን ስለ ሰማን ክንዳችን ዛለ፤ በምጥ እንደ ተያዘች ሴትም ጭንቀትና ሕመም ተሰምቶናል፤ 25ወደ እርሻ አትውጡ፤ በመንገድ ላይም አትዘዋወሩ፤ በየአቅጣጫው ሽብር ስለ ሆነ ከጠላት ሰይፍ ተጠንቀቁ።”
26እግዚአብሔር ለሕዝቡ እንዲህ ይላል፦ “ሊያጠፋችሁ የመጣው ጠላት በድንገት አደጋ ሊጥልባችሁ ስለ ሆነ፥ ማቅ ለብሳችሁ በዐመድ ላይ ተንከባለሉ፤ አንድ ልጁ እንደ ሞተበት ሰው ምርር ብላችሁ አልቅሱ፤ 27ኤርምያስ ሆይ! ብረት እንደሚፈተን ሕዝቤን ፈትነህ ምን ዐይነት እንደ ሆኑ ዕወቅ፤ 28ሁሉም እንደ ነሐስና እንደ ብረት የጠነከሩ፤ በእልህም የተወጠሩ ዐመፀኞች ናቸው። ሁሉም የተበላሹ የሐሜት ሱሰኞች ናቸው፤ 29እርሳሱን በእሳት ለማቅለጥ ወናፉ በኀይል ያናፋል፤ ክፉዎች ስላልተወገዱ ግን አንጥረኛው በከንቱ ይደክማል። 30እኔ እግዚአብሔር ስለ ጣልኳቸው ‘ንጹሕ ባለመሆኑ የወደቀ ብር’ ብለው ይጠሩአቸዋል።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ