የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኤርምያስ 51

51
በባቢሎን ላይ የሚደርስ ተጨማሪ ቅጣት
1እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ባቢሎንና ሕዝብዋን ጠራርጎ የሚያጠፋ ብርቱ ነፋስ አስነሣለሁ፤ 2እኔ እንደ እህል የሚያበጥሯትና ምድርዋን የሚያጠፉ የውጪ ጠላቶችን ወደ ባቢሎን እልካለሁ፤ እነርሱም የምትጠፉበት ጊዜ ሲደርስ ከየአቅጣጫው አደጋ ይጥሉባታል። 3ወታደሮችዋ ቀስታቸውን እስኪገትሩና ወይም የጦር ልብሳቸውን እስኪለብሱ ጊዜ አትስጡአቸው፤ ለወጣቶችዋ በመራራት ምሕረት አታድርጉ፤ ሠራዊትዋን በሙሉ ደምስሱ። 4ወታደሮችዋ በከተሞቻቸው መንገዶች ላይ ቈስለው ይሞታሉ፤ 5ምድራቸው በእኔ በእስራኤል ቅዱስ ዘንድ በበደል የተሞላች ብትሆንም እንኳ እኔ የሠራዊት ጌታ አምላካቸው እስራኤልንና ይሁዳን አልረሳኋቸውም። 6ከባቢሎን ሽሹ! ሕይወታችሁንም ለማትረፍ አምልጡ! ባቢሎን በሠራችው ኃጢአት ምክንያት በከንቱ አትለቁ! እኔ ለእርስዋ የሚገባትን ቅጣት በመስጠት የምበቀልበት ጊዜ ነው። 7መላው ዓለም ከእርስዋ ጠጥቶ ይሰክር ዘንድ ባቢሎን በእኔ እጅ እንደ ወርቅ ዋንጫ ነበረች፤ አሕዛብ ሁሉ የእርስዋን ወይን ጠጅ ጠጥተው አእምሮአቸውን ሳቱ። #ራዕ. 17፥2-4፤ 18፥3። 8ባቢሎን በድንገት ወድቃ ተሰብራለችና አልቅሱላት፤ ምናልባት ይፈወስ እንደ ሆነ ለቊስልዋ የሚቀባ መድኃኒት ፈልጉ። 9በዚያ የሚኖሩ የውጪ አገር ሰዎች እንዲህ አሉ፦ ‘ባቢሎንን ልንፈውሳት ሞከርን፤ እርሷ ግን ልትፈወስ አልቻለችም፤ የተፈረደባት ፍርድ እስከ ደመና ድረስ ከፍ ስላለና ከዚያም በላይ እስከ ሰማይ ድረስ ስለ ደረሰ ትተናት እያንዳንዳችን ወደየሀገራችን እንሂድ።’ ” #ራዕ. 18፥5።
10እስራኤላውያን እንዲህ ተባባሉ፦ “እግዚአብሔር ለእኛ ትክክለኛ ፍርዱን ስለ ሰጠን ኑ! ወደ ኢየሩሳሌም ሄደን እግዚአብሔር አምላካችን ያደረገውን ሁሉ እንናገር።”
11የእግዚአብሔር ዓላማ ስለ ቤተ መቅደሱ የበቀል ዕርምጃ ለመውሰድ ስለ ሆነ ባቢሎንን ለማጥፋት የሜዶንን ነገሥታት አነሣሥቶአል፤ ስለዚህ ፍላጻችሁን ሳሉ! ጋሻችሁንም አንሡ!
12በባቢሎን ቅጥር ላይ አደጋ ጣሉ የሚል ምልክት አሳዩ! ጥበቃውን አጠናክሩ! ሰላዮችን መድቡ! ደፈጣ ተዋጊዎችንም አዘጋጁ፤ ይህንንም የምታደርጉት እግዚአብሔር በባቢሎን ሕዝብ ላይ ያቀደውንና የተናገረውን ተግባራዊ ስለሚያደርግ ነው።
13አንቺ በታላላቅ ወንዞች አጠገብ የምትኖሪ ሀብታሚቱ ባቢሎን ሆይ! የተወሰነብሽ የመጥፊያሽ ዘመን ደርሶአል። #ራዕ. 17፥1። 14የሠራዊት አምላክ በባቢሎን ላይ ብዛቱ እንደ አንበጣ መንጋ የሆነ ሠራዊት እንደሚያመጣባት በስሙ ምሎአል፤ ያም ሠራዊት ድልን በመቀዳጀት ይደነፋል።
ለእግዚአብሔር የሚቀርብ የምስጋና መዝሙር
15እግዚአብሔር በኀይሉ ምድርን፥ በጥበቡም ዓለምን ፈጠረ፤
በማስተዋሉም ሰማያትን ዘረጋ፤
16በሰማይ ያለው ውሃ በእርሱ ትእዛዝ ይናወጣል፤
እርሱ ደመናትን ከምድር ዳርቻ ያመጣል፤
ከዝናብ ጋርም መብረቅ እንዲበርቅ ያደርጋል፤
ከማከማቻው በማውጣት ነፋስ እንዲነፍስ ያደርጋል።
17ሰዎች ሁሉ ሞኞችና አላዋቂዎች ሆኑ፤
የሠሩአቸው ምስሎች አሳፋሪ ስለ ሆኑና ሕይወትም ስለሌላቸው
አንጥረኛው በሠራቸው ጣዖቶች አፍሮባቸዋል።
18እነዚህ አማልክት ዋጋቢሶችና የፌዝ ዕቃዎች ናቸው፤
እግዚአብሔር ለፍርድ በሚገለጥበት ጊዜ ይደመሰሳሉ።
19የያዕቆብ አምላክ ግን እንደ እነርሱ አይደለም፤
እርሱ የሁሉ ነገር ፈጣሪ ነው፤
ለራሱ የተለየ ሕዝብ እንዲሆን እስራኤልን መርጦታል፤
ስሙም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው።
የእግዚአብሔር መዶሻ
20እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ባቢሎን ሆይ!
አንቺ የእኔ መዶሻና የጦር መሣሪያዬ ነበርሽ፤
በአንቺ ሕዝቦችን ለመጨፍጨፍ ተጠቅሜብሻለሁ፤
21ፈረሶችንና ፈረሰኞችን፥
ሠረገሎችንና በሠረገሎች ላይ የሚቀመጡትን ለመሰባበር ተጠቀምኩብሽ፤
22በአንቺ ሴቶችንና ወንዶችን
ሽማግሌውንና ወጣቱን፥
ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ሰባብሬአለሁ።
23እረኛውንና መንጋውን፥
ገበሬውንና ጥማድ በሬዎቹን፥
ገዢዎችንና ታላላቅ ባለሥልጣኖችን ለማጥፋት መሣሪያ አደረግሁሽ።”
የባቢሎን መቀጣት
24እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ባቢሎንና ሕዝብዋ በኢየሩሳሌም ስላደረጉት ክፉ ሥራ ሁሉ በመበቀል ብድራታቸውን ስከፍላቸው ታያላችሁ። 25ባቢሎን ሆይ! ምድርን በመላ የምታጠፊ አንቺ አጥፊ ተራራ ሆይ፥ እኔ ተቃዋሚሽ ነኝ፤ በአንቺ ላይ እጄን ዘርግቼ ከገደሉ ጫፍ ላይ አንከባልልሻለሁ፤ እንደ ተቃጠለ ተራራም አደርግሻለሁ። 26ለማእዘን ወይም ለመሠረት የሚያገለግል ድንጋይ አይገኝብሽም፥ አንቺ ለዘለዓለሙ ምድረ በዳ ትሆኚአለሽ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።
27“አደጋ ለመጣል የሚያስችል ምልክት ስጡ! ሕዝቦች ሁሉ መስማት እንዲችሉ እምቢልታ ንፉ! ባቢሎንን ይወጉ ዘንድ ሕዝቦችን አዘጋጁ! የአራራት፥ የሚኒና የአሽኬናዝ መንግሥታት አደጋ እንዲጥሉ ንገሩአቸው፤ የጦር አዛዥ የሚሆን ሰው ሹሙ፤ ብዛታቸው እንደ አንበጣ መንጋ የሆነ ፈረሶችን አምጡ። 28ባቢሎንን ይወጉ ዘንድ ሕዝቦችን አዘጋጁ፤ መድቡ፤ ወደ ሜዶን ነገሥታት፥ ወደ መሪዎቻቸውና ጦር አዛዦቻቸው እንዲሁም እነርሱ በሚቈጣጠሩአቸው አገሮች ወደሚኖሩ ሠራዊት ሁሉ መልእክት ላኩ። 29ባቢሎንን ማንም የማይኖርባት ምድረ በዳ እንድትሆን ለማድረግ እግዚአብሔር ያቀደውን የሚፈጽምበት ጊዜ ከመሆኑ የተነሣ፥ ምድር በመናወጥ ትንቀጠቀጣለች። 30የባቢሎን ወታደሮች ጦርነቱን አቁመው በምሽጋቸው ተቀመጡ፤ የጀግንነትን ወኔ አጥተው እንደ ሴቶች ሆኑ፤ የከተማይቱ የቅጽር በሮች መወርወሪያዎች ተሰባብረዋል፤ ቤቶችም በእሳት ተቃጥለዋል። 31የእርሱ ከተማ ከዳር እስከ ዳር የተያዘች መሆንዋን ለባቢሎን ንጉሥ ለመንገር አንዱ ሩዋጭ ለሌላው ሩዋጭ፥ አንዱ መልእክተኛ ለሌላው መልእክተኛ መልእክቱን ለማስተላለፍ ይሯሯጣሉ። 32የጠላት ሠራዊት የወንዙን መሸጋገሪያ ይዞ የዘብ መጠበቂያዎቹን አቃጠለ፤ የባቢሎን ወታደሮች በመሸበር ተርበደበዱ፤ 33ባቢሎን እንደ እህል መውቂያ አውድማ ትሆናለች፤ ሕዝብዋንም እንደሚወቃ እህል ጠላት ያበራያቸዋል። እኔ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ ይህን ተናግሬአለሁ።” 34የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ኢየሩሳሌምን በዘበዘ አደቀቃትም እንደ ባዶ ዕቃም አደረጋት፤ እንደ ዘንዶ ሕዝብዋን ዋጠ፤ ምርጥ ምርጡን ወስዶ የቀሩትን እንደሚተፋ ምግብ ጣላቸው።
35ስለዚህ የጽዮን ከተማ ሕዝብ “በእኛ ላይ የደረሰው
ሥቃይ በባቢሎን ላይ ይድረስ!” ይላሉ፤
የኢየሩሳሌምም ሕዝብ “የእኛ ደም
እንደ ፈሰሰ የባቢሎናውያንም ደም ይፍሰስ!” ይላሉ።
36ስለዚህ እግዚአብሔር ለኢየሩሳሌም ሕዝብ እንዲህ ይላል፦ “እኔ እናንተን እረዳለሁ፤ ባቢሎናውያንንም እበቀልላችኋለሁ፤ የባቢሎን የውሃ ምንጭና ወንዞችዋ ሁሉ እንዲደርቁ አደርጋለሁ። 37ያቺ አገር የፍርስራሽ ክምርና የቀበሮዎች መፈንጫ ትሆናለች፤ ለማየትም የምታሰቅቅ ትሆናለች፤ ማንም አይኖርባትም፤ የሚያያትም ሁሉ ይሳለቅባታል። 38ባቢሎናውያን ሁሉ እንደ አንበሳ ያገሣሉ፤ እንደ አንበሳ ደቦልም ያጒረመርማሉ። 39ሞቅ ባላቸው ጊዜ የመጠጥ ግብዣ አደርግላቸዋለሁ፤ እስኪሰክሩ ድረስም አጠጣቸዋለሁ፤ ከዚያም ዘለዓለማዊ እንቅልፍ ያንቀላፋሉ፤ እስከ መቼም አይነቁም። 40እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እንደ በግ ጠቦቶችና እንደ አውራ ፍየሎች ወደ ዕርድ ቦታ እንዲወሰዱ አደርጋቸዋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”
41እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የባቢሎን ከተማ እንዴት ተወረረች! ያቺ የዓለም መመኪያ የነበረችው እርስዋ እንዴት ተያዘች! ባቢሎንስ በሕዝብ ዘንድ ምንኛ አስደንጋጭ ሆነች! 42የባቢሎን ጠላቶች እንደ ውቅያኖስ ማዕበል ወጥተው ከተማይቱን አጥለቀለቋት። 43ከተሞቹ ውሃ የማይገኝባቸውና ማንም ሊኖርባቸውም ሆነ ሊተላለፍባቸው የማይችል ምድረ በዳ ሆነዋል። 44የባቢሎን ጣዖት የሆነውን ቤልን እቀጣለሁ፤ የተሰረቁ ዕቃዎቹንም ከእጁ አስጥላለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህም አሕዛብ አይሰግዱለትም።”
“የባቢሎን ቅጽሮች ወድቀዋል፤ 45ሕዝቤ ሆይ! ከዚያ ሸሽታችሁ ውጡ! ከሚያስፈራውም ቊጣዬ ሕይወታችሁን ለማትረፍ አምልጡ! 46ከምትሰሙትም የጒምጒምታ ወሬ የተነሣ በመፍራት ወኔአችሁ አይቀዝቅዝ፤ በየዓመቱ ልዩ ልዩ የጒምጒምታ ወሬ ይነዛል፤ በምድሪቱ ላይ አንዱ ንጉሥ ሌላውን እንደሚወጋ የሚገልጥ የዐመፅ ጒምጒምታ ወሬ ይሰማል። 47ስለዚህም የባቢሎንን ጣዖቶች የማስወግድበት ጊዜ ይመጣል፤ በምድሪቱ ሁሉ ላይ ኀፍረት ይደርሳል፤ የተገደሉባት ልጆችዋ ሁሉ በመካከልዋ ይወድቃሉ። 48ባቢሎን ከሰሜን በሚመጡ አጥፊዎች እጅ በወደቀች ጊዜ በሰማይና በምድር የሚገኝ ሠራዊት ሁሉ በደስታ እልል ይላል። #ራዕ. 18፥20። 49ባቢሎን ለዓለም ሕዝብ እልቂት ምክንያት ሆናለች፤ ለብዙ እስራኤላውያን እልቂት ምክንያት በመሆንዋም እነሆ ባቢሎን ራስዋ መውደቅ አለባት፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።” #ራዕ. 18፥24።
በባቢሎን ላሉት እስራኤላውያን የተላከ መልእክት
50እግዚአብሔር በባቢሎን ላሉት ሕዝብ እንዲህ ይላል፦ “እናንተ ከሞት የተረፋችሁ ሕዝቤ! ሳትዘገዩ ሂዱ! በሩቅ ሀገር ሆናችሁ እኔን እግዚአብሔርን አስታውሱ! ኢየሩሳሌምን በልባችሁ አስቡ! 51‘ስለ ተሰደብን አፈርን፤ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ ወደ ተቀደሱ ስፍራዎች ባዕዳን ሰዎች ስለ ገቡ ተዋርደን አንገታችንን ደፋን።’ በሉ። 52እኔ እግዚአብሔር የምለው ይህ ነው። በባቢሎን ጣዖቶች ላይ የምፈርድበትና በሀገሪቱም የሚገኙ ቊስለኞች የጭንቀት ድምፅ የሚያሰሙበት ጊዜ ይመጣል፤ 53ባቢሎን ወደ ሰማይ ብትወጣ ከፍተኛውን ምሽግዋን ብታጠናክር እንኳ የሚደመስሳትን አጥፊ እልካለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”
በባቢሎን ላይ የሚደርስ ተጨማሪ ጥፋት
54እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ከባቢሎን ጩኸት፥
ከከለዳውያን ምድርም የታላቅ ጥፋት ድምፅ ይሰማል።
55እንደ ባሕር ሞገድ የሚያስገመግም ሠራዊት በድንገት በባቢሎን ላይ ደርሶ
እየደነፋ አደጋ ይጥልባታል፤
በዚህም እኔ አጠፋታለሁ፤ ጸጥም አደርጋታለሁ።
56አጥፊዎች በባቢሎን ላይ ስለ ዘመቱ
ወታደሮችዋ ተማረኩ፤
ቀስታቸውም ተሰባበረ፤
እኔ ለሁሉም እንደየሥራው ዋጋውን የምከፍል አምላክ ስለ ሆንኩ፥
ባቢሎን በፈጸመችው ግፍ መጠን ፍዳዋን እከፍላታለሁ።
57መሳፍንትዋ፥ የጥበብ ሰዎችዋ፥ መሪዎችዋ፥ የጦር አዛዦችዋና ወታደሮችዋ
ጠጥተው እንዲሰክሩ አደርጋለሁ፤
ከዚያም በኋላ ይተኛሉ፤ እስከ ዘለዓለም አይነቁም፤
ይህን የተናገርኩ እኔ ንጉሡ ነኝ፤ ስሜም የሠራዊት አምላክ ነው።
58ሰፊው የባቢሎን ቅጽር ወድቆ ከመሬት ይደባለቃል፤
ከፍ ብለው የተሠሩ የቅጽር በሮችዋ በእሳት ይጋያሉ።
የሕዝብዋ ድካም ከንቱ ይሆናል፤
ሕዝቦች የደከሙበት ነገር ሁሉ በእሳት ይወድማል።
እኔ የሠራዊት አምላክ ይህን ተናግሬአለሁ።”
ኤርምያስ ወደ ባቢሎን የላከው መልእክት
59የማሕሴያ የልጅ ልጅ የሆነው የኔሪያ ልጅ ሠራያ የንጉሥ ሴዴቅያስ የቅርብ አገልጋይ ነበር፤ ሴዴቅያስ በይሁዳ በነገሠ በአራተኛው ዓመት፥ ሠራያ ከእርሱ ጋር ወደ ባቢሎን ወረደ፤ እኔም ኤርምያስ በዚያን ጊዜ መመሪያዎችን ሰጠሁት፤ 60በባቢሎን ላይ የሚመጣውን ጥፋት እንዲሁም ስለ እርስዋ የተነገረውን ቃል በመጽሐፍ ጻፍኩ፤ 61ሠራያንም እንዲህ አልኩት “ባቢሎን እንደ ደረስህ በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን ሁሉ ድምፅህን ከፍ አድርገህ ለሕዝቡ አንብብላቸው፤ 62ከዚያም በኋላ ‘ጌታ ሆይ! አንተ ይህን ስፍራ እንደምታጠፋ ተናግረሃል፤ ስለዚህም ሕይወት ያለው ተንቀሳቃሽ ፍጥረት አይኖርባትም፤ ሰውም እንስሳም ስለሚጠፋ ለዘለዓለም ምድረ በዳ ሆና ትቀራለች’ በል። 63ሠራያ ሆይ! ይህን መጽሐፍ ለሕዝቡ አንብበህ ከጨረስክ በኋላም መጽሐፉን ከድንጋይ ጋር አስረህ ወደ ኤፍራጥስ ወንዝ ወርውረህ ጣለው። 64እንዲህም በል፦ ‘ባቢሎንም እንደዚሁ እግዚአብሔር በእርስዋ ላይ ከሚያመጣው ጥፋት የተነሣ ወድቃ ትቀራለች እንጂ እንደገና መነሣት አትችልም።’ ” #ራዕ. 18፥21።
ኤርምያስ የተናገረው ቃል እዚህ ላየ ተፈጸመ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ