የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኤርምያስ 23:1-8

ትንቢተ ኤርምያስ 23:1-8 አማ05

“የእግዚአብሔር መንጋ የሆነውን ሕዝብ ለሚበትኑና ለሚያጠፉ መሪዎች ወዮላቸው!” ይላል እግዚአብሔር፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የሕዝቡ ጠባቂዎች መሆን ስለሚገባቸው መሪዎች እንዲህ ይላል፦ “ሕዝቤን እንደሚገባ አልጠበቃችሁም፤ ይልቁንም አሳዳችሁ በተናችሁ፤ ስለዚህ ስለ ፈጸማችሁት ክፋት ሁሉ እቀጣችኋለሁ። የቀሩትን ሕዝቤን ከበተንኳቸው አገር ሁሉ ሰብስቤ ወደ ትውልድ አገራቸው እመልሳቸዋለሁ፤ ብዙ ልጆች ስለሚወልዱ ቊጥራቸው እየጨመረ ይሄዳል። የሚጠብቁአቸውን መሪዎች እሾምላቸዋለሁ፤ ሕዝቤ ከእንግዲህ ወዲህ ያለ ፍርሀትና ያለ ድንጋጤ ይኖራሉ፤ እኔም ዳግመኛ አልቀጣቸውም፤ ወይም ከእነርሱ አንድም አይጐድልም፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ከዳዊት ዘር መካከል ጻድቅ የሆነውን ለንጉሥነት የምመርጥበት ጊዜ ይመጣል፤ ያም ንጉሥ በጥበብ ያስተዳድራል፤ በምድሪቱም ሁሉ ላይ ትክክልና ቅን የሆነውን ነገር ያደርጋል። እርሱ በሚነግሥበት ጊዜ የይሁዳ ሕዝብ ደኅንነት ያገኛል፤ የእስራኤልም ሕዝብ በሰላም ይኖራል፤ እርሱም ‘እግዚአብሔር ጽድቃችን’ ተብሎ ይጠራል። “ሰዎች ‘የእስራኤልን ሕዝብ ከግብጽ ምድር ያወጣ ሕያው እግዚአብሔርን’ ብለው የማይምሉበት ጊዜ ይመጣል። በዚህ ፈንታ፥ የእስራኤልን ሕዝብ ከሰሜን ምድርና ተበታትነው ከነበሩባቸው ሌሎች አገሮች ሰብስቤ ባመጣኋቸው በእኔ በሕያው እግዚአብሔር ስም ይምላሉ፤ ከዚያም በኋላ በገዛ ምድራቸው ይኖራሉ።”