እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የይሁዳ ሕዝብ ሆይ! ኃጢአታችሁ በብረት ብዕር ተጽፎአል፤ ሹል በሆነው አልማዝ በልባችሁ ጽላትና በመሠዊያዎቻችሁ ቀንዶች ላይ ተቀርጾአል። በመላ አገራችሁ፥ በኮረብቶችና በተራሮች ላይ እንዲሁም በታላላቅ ዛፎች ሥር ሕዝቡ በየትውልዱ መሠዊያዎችንና የተለዩ ዐምዶችን አቁሞ አሼራ ተብላ ለምትጠራው ጣዖት ይሰግዳሉ። በመላ አገራችሁ በፈጸማችሁት ከፍተኛ ኃጢአት ምክንያት ያላችሁን ሀብትና ንብረት እንዲሁም መሠዊያዎቻችሁን ሁሉ በምርኮ ጠላቶቻችሁ እንዲወስዱ አደርጋለሁ። ቊጣዬ እንደ እሳት እንዲቀጣጠል ስላደረጋችሁ እርሱም ለዘለዓለም ስለሚነድ የሰጠኋችሁን ርስት ሁሉ እንድታጡና በማታውቁት አገር ጠላቶቻችሁን እንድታገለግሉ አደርጋለሁ።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እኔን ትቶ በሰው የሚታመንና፥ ‘ኀይል ይሆነኛል’ ብሎ በሥጋ ለባሽ ሰው የሚመካ የተረገመ ይሁን። እንዲህ ዐይነቱ ሰው ማንም ሊኖርበት በማይችል በጨው ምድርና በበረሓ እንደሚበቅል ቊጥቋጦ ነው፤ በሕይወቱ ሙሉ ምንም መልካም ነገርን አያገኝም። “በእኔ ብቻ ተማምኖ የሚኖር ሰው ግን የተባረከ ነው። እርሱም በወራጅ ምንጭ አጠገብ እንደ ተተከለና በውሃም ውስጥ ሥር እንደ ሰደደ ዛፍ ይሆናል፤ ዘወትር ቅጠሉ ለምለም ሆኖ የሚኖር ይህ ዐይነቱ ዛፍ የፀሐይ ሐሩር እንኳ አያሰጋውም፤ ዝናብ ባይዘንብለትም እንኳ ፍሬ ከማፍራት አይገታም። “የሰው ልብ ከሁሉ ነገር በላይ ተንኰለኛና ጠማማ ነው፤ ውስጠ ምሥጢሩን የሚረዳ ማነው? እኔ እግዚአብሔር ግን የሰውን አእምሮና የሰውን ልብ እመረምራለሁ፤ እያንዳንዱንም ሰው በአካሄዱና በሥራው መጠን ዋጋውን እሰጠዋለሁ።” ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ሀብትን የሚሰበስብ፥ ያልጣለችውን ዕንቊላል ታቅፋ እንደምትፈለፍል ቆቅ ነው፤ በዕድሜው አጋማሽ የሰበሰበውን ሃብት ሁሉ ያጣል። በመጨረሻም ሞኝነቱ ግልጥ ይሆናል። ቤተ መቅደሳችን የተሠራበት ቦታ ከመጀመሪያው ጀምሮ ከፍ እንዳለው የክብር ዙፋን ነው። እግዚአብሔር ሆይ! አንተ የእስራኤል ተስፋ ነህ፤ አንተን የሚተዉ ሁሉ ያፍራሉ፤ የሕይወት ውሃ ምንጭ የሆንከውን አንተን እግዚአብሔርን ስለ ተዉ በትቢያ ላይ እንደ ተጻፈ ስም ይደመሰሳሉ። እግዚአብሔር ሆይ፥ ፈውሰኝ፤ እኔም እፈወሳለሁ፤ ታደገኝ፤ እኔም በሰላም እኖራለሁ፤ ዘወትርም አንተን አመሰግናለሁ። ሕዝቡ “ኤርምያስ ሆይ! እግዚአብሔር ተናገረ ያልከውን ነግረኸን ነበር፤ ታዲያ ለምን አልተፈጸመም” ብለው ይጠይቁኛል። ነገር ግን እግዚአብሔር ሆይ! በእነርሱ ላይ መቅሠፍትን እንድታመጣ ያሳሰብኩህ ጊዜ የለም፤ የመከራ ዘመን እንዲገጥማቸውም አልተመኘሁም፤ እግዚአብሔር ሆይ! አንተ ይህንና የተናገርኩትን ሁሉ ታውቃለህ። አንተ በመከራ ጊዜ መሸሸጊያዬ ስለ ሆንክ አስደንጋጭ አትሁንብኝ፤ እግዚአብሔር ሆይ! በሚያሳድዱኝ ሁሉ ላይ ኀፍረትን አምጣባቸው፤ እኔን ግን አታሳፍረኝ፤ እነርሱ እንዲሸበሩ አድርግ፤ እኔን ግን አታስደንግጠኝ፤ ተሰባብረው እስኪደቁ ድረስ ደጋግመህ አጥፋቸው።
ትንቢተ ኤርምያስ 17 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ ኤርምያስ 17:1-18
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos