ትንቢተ ኤርምያስ 17
17
የይሁዳ ሕዝብ ኃጢአትና የደረሰባቸው ቅጣት
1እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የይሁዳ ሕዝብ ሆይ! ኃጢአታችሁ በብረት ብዕር ተጽፎአል፤ ሹል በሆነው አልማዝ በልባችሁ ጽላትና በመሠዊያዎቻችሁ ቀንዶች ላይ ተቀርጾአል። 2በመላ አገራችሁ፥ በኮረብቶችና በተራሮች ላይ እንዲሁም በታላላቅ ዛፎች ሥር ሕዝቡ በየትውልዱ መሠዊያዎችንና የተለዩ ዐምዶችን አቁሞ አሼራ ተብላ ለምትጠራው ጣዖት ይሰግዳሉ። 3በመላ አገራችሁ በፈጸማችሁት ከፍተኛ ኃጢአት ምክንያት ያላችሁን ሀብትና ንብረት እንዲሁም መሠዊያዎቻችሁን ሁሉ በምርኮ ጠላቶቻችሁ እንዲወስዱ አደርጋለሁ። 4ቊጣዬ እንደ እሳት እንዲቀጣጠል ስላደረጋችሁ እርሱም ለዘለዓለም ስለሚነድ የሰጠኋችሁን ርስት ሁሉ እንድታጡና በማታውቁት አገር ጠላቶቻችሁን እንድታገለግሉ አደርጋለሁ።”
ልዩ ልዩ ምሳሌዎች
5እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
“እኔን ትቶ በሰው የሚታመንና፥
‘ኀይል ይሆነኛል’ ብሎ በሥጋ ለባሽ ሰው የሚመካ የተረገመ ይሁን።
6እንዲህ ዐይነቱ ሰው
ማንም ሊኖርበት በማይችል በጨው ምድርና
በበረሓ እንደሚበቅል ቊጥቋጦ ነው፤
በሕይወቱ ሙሉ ምንም መልካም ነገርን አያገኝም።
7“በእኔ ብቻ ተማምኖ የሚኖር ሰው ግን የተባረከ ነው።
8እርሱም በወራጅ ምንጭ አጠገብ እንደ ተተከለና
በውሃም ውስጥ ሥር እንደ ሰደደ ዛፍ ይሆናል፤
ዘወትር ቅጠሉ ለምለም ሆኖ የሚኖር ይህ ዐይነቱ ዛፍ
የፀሐይ ሐሩር እንኳ አያሰጋውም፤
ዝናብ ባይዘንብለትም እንኳ ፍሬ ከማፍራት አይገታም። #መዝ. 1፥3።
9“የሰው ልብ ከሁሉ ነገር በላይ
ተንኰለኛና ጠማማ ነው፤
ውስጠ ምሥጢሩን የሚረዳ ማነው?
10እኔ እግዚአብሔር ግን የሰውን አእምሮና
የሰውን ልብ እመረምራለሁ፤
እያንዳንዱንም ሰው በአካሄዱና በሥራው መጠን ዋጋውን እሰጠዋለሁ።” #መዝ. 62፥12፤ ራዕ. 2፥23።
11ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ሀብትን የሚሰበስብ፥
ያልጣለችውን ዕንቊላል ታቅፋ እንደምትፈለፍል ቆቅ ነው፤
በዕድሜው አጋማሽ የሰበሰበውን ሃብት ሁሉ ያጣል።
በመጨረሻም ሞኝነቱ ግልጥ ይሆናል።
12ቤተ መቅደሳችን የተሠራበት ቦታ
ከመጀመሪያው ጀምሮ ከፍ እንዳለው የክብር ዙፋን ነው።
13እግዚአብሔር ሆይ! አንተ የእስራኤል ተስፋ ነህ፤
አንተን የሚተዉ ሁሉ ያፍራሉ፤
የሕይወት ውሃ ምንጭ የሆንከውን አንተን እግዚአብሔርን ስለ ተዉ
በትቢያ ላይ እንደ ተጻፈ ስም ይደመሰሳሉ።
ኤርምያስ እግዚአብሔር እንዲታደገው መለመኑ
14እግዚአብሔር ሆይ፥ ፈውሰኝ፤ እኔም እፈወሳለሁ፤ ታደገኝ፤ እኔም በሰላም እኖራለሁ፤ ዘወትርም አንተን አመሰግናለሁ። 15ሕዝቡ “ኤርምያስ ሆይ! እግዚአብሔር ተናገረ ያልከውን ነግረኸን ነበር፤ ታዲያ ለምን አልተፈጸመም” ብለው ይጠይቁኛል።
16ነገር ግን እግዚአብሔር ሆይ! በእነርሱ ላይ መቅሠፍትን እንድታመጣ ያሳሰብኩህ ጊዜ የለም፤ የመከራ ዘመን እንዲገጥማቸውም አልተመኘሁም፤ እግዚአብሔር ሆይ! አንተ ይህንና የተናገርኩትን ሁሉ ታውቃለህ። 17አንተ በመከራ ጊዜ መሸሸጊያዬ ስለ ሆንክ አስደንጋጭ አትሁንብኝ፤ 18እግዚአብሔር ሆይ! በሚያሳድዱኝ ሁሉ ላይ ኀፍረትን አምጣባቸው፤ እኔን ግን አታሳፍረኝ፤ እነርሱ እንዲሸበሩ አድርግ፤ እኔን ግን አታስደንግጠኝ፤ ተሰባብረው እስኪደቁ ድረስ ደጋግመህ አጥፋቸው።
ሰንበትን ስለማክበር
19እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “የይሁዳ ንጉሥ ከከተማይቱ በሚወጣበትና በሚገባበት ወደ ሕዝቡ ቅጽር በር እንዲሁም በኢየሩሳሌም ወደሚገኙት ወደ ሌሎቹም ቅጽር በሮች ሄደህ ቁም፤ 20እኔ የምነግርህንም ቃል እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘የይሁዳ ነገሥታትና ሕዝብ! እንዲሁም በእነዚህ ቅጽር በሮች የምትገቡ የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ሆይ! የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ! 21ሕይወታችሁን ለማዳን እኔ የምሰጣችሁን ማስጠንቀቂያ ጠብቁ፤ ስለዚህ በሰንበት ቀን ምንም ዐይነት ሸክም ተሸክማችሁ በኢየሩሳሌም ቅጽር በሮች አትግቡ። #ነህ. 13፥15-22። 22የቀድሞ አባቶቻችሁን እንዳዘዝኳቸው ሰንበትን የተቀደሰ ቀን አድርጋችሁ አክብሩ እንጂ በሰንበት ቀን ሸክም ተሸክማችሁ ከቤታችሁ አትውጡ፤ በሰንበት ቀን ምንም ሥራ አትሥሩ። #ዘፀ. 20፥8-10፤ ዘዳ. 5፥12-14። 23የቀድሞ አባቶቻችሁ ቃሌን አላዳመጡም፤ ትእዛዜንም አልፈጸሙም፤ ይልቁንም እልኸኞች በመሆን ለእኔ መታዘዝንና ከእኔ መማርን እምቢ አሉ።
24“‘እንግዲህ የሚያዳምጡኝ ከሆኑ እነዚህ ሕዝብ ትእዛዜን እንዲጠብቁ ንገራቸው፤ በሰንበት ቀን ምንም ዐይነት ሸክም ይዘው በከተማይቱ በሮች አይግቡ፤ ሰንበትን የተቀደሰ ቀን አድርገው ያክብሩ እንጂ በዚያን ቀን ምንም ሥራ አይሥሩ። 25በዳዊት ዙፋን ላይ የተቀመጡ ነገሥታት ከባለ ሥልጣኖቻቸው ጋር በኢየሩሳሌም በሮች ይገባሉ፤ እነርሱም ከይሁዳና ከኢየሩሳሌም ሕዝብ ጋር በአንድነት ሆነው በፈረሶችና በሠረገሎች ላይ ይቀመጣሉ፤ የኢየሩሳሌም ከተማ ሁልጊዜ በሕዝብ የተሞላች ትሆናለች። 26ከይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም ዙሪያ ከሚገኙ መንደሮች ሕዝቡ በአንድነት ይሰበሰባሉ፤ ከብንያም ክፍል፥ ከኰረብቶች ግርጌ፥ ከተራሮችና ከይሁዳ ደቡብ ይመጣሉ፤ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ሌላውንም መሥዋዕት፥ የእህል ቊርባንና ዕጣን፥ የምስጋናውንም መሥዋዕት ጭምር ወደ ቤተ መቅደሴ ያመጣሉ። 27ነገር ግን ለእኔ መታዘዝና ሰንበትንም የተቀደሰ ቀን አድርገው ማክበር ይገባቸዋል፤ በዚህ ዕለት በኢየሩሳሌም የቅጽር በሮች ምንም ዐይነት ሸክም ይዘው መግባት የለባቸውም፤ ትእዛዜን ባለመቀበል ይህን ቢያደርጉ ግን የኢየሩሳሌም ቅጽር በሮች በእሳት እንዲጋዩ አደርጋለሁ፤ የኢየሩሳሌም ቤተ መንግሥቶችም በእሳት ይነዳሉ፤ እሳቱንም ሊያጠፋ የሚችል የለም።’ ”
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 17: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997