የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኤርምያስ 16

16
ስለ ኤርምያስ ሕይወት የእግዚአብሔር ፈቃድ
1እግዚአብሔር እንደገና እንዲህ አለኝ፦ 2“በዚህ ባለው ቦታ ሚስት አታግባ፤ ልጆችም አትውለድ፤ 3በዚህ ስፍራ በሚወለዱ ልጆችና እነርሱንም በሚወልዱአቸው ወላጆች ላይ የሚደርስባቸውን እነግርሃለሁ፤ 4ሁሉም በአሠቃቂ በሽታ ያልቃሉ፤ የሚያለቅስላቸውም ሆነ የሚቀብራቸው እንኳ አያገኙም፤ ሬሳቸው እንደ ጒድፍ በሜዳ ላይ ይከመራል፤ በጦርነትና በራብ ያልቃሉ፤ ሬሳቸውም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት ምግብ ይሆናል።
5“ለቅሶ ወዳለበት ቤት አትግባ፤ ስለ ማንም ሐዘንህን አትግለጥ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሕዝቤን በሰላም አልባርክም፤ ዘላቂ ፍቅርና ምሕረትም አላሳያቸውም፤ 6በዚህች ምድር የሚገኙ ሀብታሞችም ድኾችም ሁሉ ይሞታሉ፤ አልቅሶ የሚቀብራቸውም አያገኙም፤ ስለ እነርሱ ሐዘኑን ለመግለጥ ፊቱን የሚነጭም ሆነ ጠጒሩን የሚላጭ አይኖርም። 7ወዳጁ የሞተበትን ሰው ለማጽናናት የእዝን እንጀራ በመውሰድ አብሮት የሚበላና የሚጠጣ አይኖርም፤ ሌላው ቀርቶ እናትም አባትም የሞቱበትን የሚያጽናና አይገኝም።
8“ሰዎች ወደሚደሰቱበት ግብዣ ቤትም አትግባ፤ ለመብላትና ለመጠጣትም ከእነርሱ ጋር አትቀመጥ። 9እኔ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ የምልህን አድምጥ፥ አንተ ባለህበት በዚህ ዘመን የደስታና የሐሤት፥ የሠርግ ዘፈን ድምፅ እንዳይሰማ አደርጋለሁ። #ኤር. 7፥34፤ 25፥10፤ ራዕ. 18፥23።
10“ይህን ሁሉ በምትነግራቸው ጊዜ ‘እግዚአብሔር በእኛ ላይ ይህን የሚያኽል ከባድ ጥፋት ለምን ወሰነብን? ምን በደልን? በአምላካችን በእግዚአብሔር ፊትስ የሠራነው ኃጢአት ምንድን ነው?’ ብለው ይጠይቁሃል። 11በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር እንዲህ ይላችኋል በላቸው፦ ‘የቀድሞ አባቶቻችሁ ከእኔ ተለይተው የሐሰት አማልክትን በማምለክ አገለገሉ፤ እኔን ተዉኝ፤ ሕጌንም አልፈጸሙም። 12እናንተ ደግሞ ከቀድሞ አባቶቻችሁ የባሰ ክፉ ነገር አደረጋችሁ፤ ሁላችሁም እልኸኞችና ዐመፀኞች ሆናችሁ፤ ለእኔም አትታዘዙም። 13ስለዚህ ከዚህች አገር አውጥቼ፥ እናንተም ሆናችሁ የቀድሞ አባቶቻችሁ ወደማያውቁት አገር እወረውራችኋለሁ፤ እዚያም ሐሰተኞች አማልክትን ቀንና ሌሊት ታመልካላችሁ፤ ፈጽሞ ምሕረት አላደርግላችሁም።’ ”
የእስራኤል ሕዝብ ከምርኮ መመለስ
14እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ ‘የእስራኤልን ሕዝብ ከግብጽ ያወጣ ሕያው እግዚአብሔርን’ ብለው የማይምሉበት ጊዜ ይመጣል፤ 15በዚህ ፈንታ ‘የእስራኤልን ሕዝብ ከሰሜን አገርና ከሌሎችም እነርሱን ከበተነበት አገር ሁሉ ያስወጣ ሕያው እግዚአብሔርን’ ብለው ይምላሉ፤ ወደገዛ አገራቸውና ለቀድሞ አባቶቻቸው ወደ ሰጠኋቸው ምድር መልሼ አመጣቸዋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”
የሚመጣው ቅጣት
16እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ይህን ሕዝብ እንደ ዓሣ የሚያጠምዱና እንደ አውሬ የሚያድኑ ብዙ ሰዎችን እልካለሁ፤ በየተራራውና በየኰረብታው በቋጥኞች ውስጥ ባሉ ዋሻዎችም እያደኑ ይይዙአቸዋል። 17የሚያደርጉትን ሁሉ አያለሁ፤ ከእኔ የሚሰወር ምንም ነገር የለም፤ ኃጢአታቸው ሁሉ በፊቴ የተገለጠ ነው። 18እንደ በድን ሕይወት በሌላቸው ጣዖቶች ርስቴን ስላረከሱና በሐሰተኞች አማልክታቸው ስለ ሞሉአት ስለ ኃጢአታቸውና ስለ ክፋታቸው በእጥፍ እቀጣቸዋለሁ።”
የኤርምያስ ጸሎት
19እግዚአብሔር ሆይ! የምትጠብቀኝና ብርታትን የምትሰጠኝ አንተ ነህ፤ በመከራም ጊዜ መጠጊያ አምባዬ ነህ፤ ሕዝቦች ከምድር ዳርቻ ሁሉ ወደ አንተ መጥተው እንዲህ ይላሉ፦ “የቀድሞ አባቶቻችን ከሐሰተኞች አማልክት በቀር ምንም አልነበራቸውም፤ ጣዖቶቻቸው ሁሉ የማይጠቅሙ ከንቱዎች ነበሩ፤ 20ለመሆኑ ሰው የራሱን አማልክት መሥራት ይችላልን? አዎ፥ ግን እውነተኛ አምላክነት የላቸውም።
21“ስለዚህ ሕዝቦች በሙሉ ኀይሌንና ታላቅነቴን በማያዳግም ሁኔታ እንዲያውቁት አደርጋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር መሆኔንም ያረጋግጣሉ።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ