ትንቢተ ኤርምያስ 11
11
ኤርምያስና የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን
1ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣ ቃል የሚከተለው ነው፤ 2“የዚህን ቃል ኪዳን ይዘት አድምጠህ ለይሁዳ ሕዝብና ለኢየሩሳሌም ከተማ ነዋሪዎች ንገራቸው። 3ይህን ቃል ኪዳን የማይታዘዝ ሁሉ የተረገመ ይሁን። 4ይህ ቃል ኪዳን እንደ ጋለ ምድጃ ከሆነችባቸው አገር ከግብጽ ባወጣኋቸው ጊዜ ለቀድሞ አባቶቻችሁ የሰጠሁት ነው፤ ለእኔ እንዲታዘዙና እኔ የምላቸውን ሁሉ እንዲፈጽሙ ነገርኳቸው፤ የሚታዘዙኝም ከሆነ እነርሱ ሕዝቤ እንደሚሆኑና እኔም አምላካቸው እንደምሆን ገለጥኩላቸው። 5ይህም ከሆነ አሁን ያሉባትን በማርና በወተት የበለጸገችውን ለምለም ምድር የቀድሞ አባቶቻቸው እንዲወርሱ ባደረግሁ ጊዜ የሰጠኋቸውን የተስፋ ቃል እፈጽማለሁ።”
እኔም “እሺ ጌታ ሆይ!” አልኩ።
6ከዚያን በኋላም እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “ወደ ይሁዳ ከተሞችና ወደ ኢየሩሳሌም መንገዶች ሄደህ ቃል ኪዳኔን እንዲያዳምጡና ትእዛዞቼን እንዲፈጽሙ በማሳሰብ ቃሌን ዐውጅላቸው፤ 7የቀድሞ አባቶቻቸውን ከግብጽ ባወጣኋቸው ጊዜ ለእኔ እንዲታዘዙ ደጋግሜ አስጠነቀቅኋቸው፤ ሕዝቡንም እስከ ዛሬው ቀን ድረስ እንኳ ከማስጠንቀቅ አልተቈጠብኩም። 8ነገር ግን ሊያዳምጡኝም ሆነ ሊታዘዙኝ አልፈለጉም፤ በዚህ ፈንታ እያንዳንዱ ከምንጊዜውም ይልቅ እልኸኛና ክፉ ሆኖአል፤ ቃል ኪዳኔን እንዲፈጽሙ አዘዝኳቸው፤ እነርሱ ግን እምቢ አሉ፤ ስለዚህ በቃል ኪዳኔ የተጻፈውን መቅሠፍት ሁሉ አመጣሁባቸው።”
9ቀጥሎም እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብ በኔ ላይ ዐድመዋል፤ 10እኔ ያዘዝኳቸውን ለመፈጸም እምቢ ይሉ እንደ ነበሩት እንደ ቀድሞ አባቶቻቸው ኃጢአት ይሠራሉ፤ ባዕዳን አማልክትን ያመልካሉ፤ እስራኤልና ይሁዳ በአንድነት ከቀድሞ አባቶቻቸው ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን አፍርሰዋል። 11ስለዚህም እነሆ እኔ እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ጥፋት አመጣባቸዋለሁ፤ ከጥፋቱም ማምለጥ አይችሉም፤ የእኔን ርዳታ ለማግኘት ቢጮኹም እንኳ አልሰማቸውም። 12በዚያን ጊዜ የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብ መሥዋዕት ወደሚያቀርቡላቸው ባዕዳን አማልክት ሄደው ርዳታ እንዲያደርጉላቸው ይጮኻሉ፤ ነገር ግን እነርሱ ይህ ጥፋት በሚመጣበት ጊዜ ሊያድኑአቸው አይችሉም። 13የይሁዳ ሕዝብ ሆይ፥ በከተሞቻችሁ ልክ ብዙ አማልክት አሉአችሁ፤ በኢየሩሳሌምም መንገዶች ልክ አጸያፊ ለሆነው በዓል ተብሎ ለሚጠራው ባዕድ አምላክ መሥዋዕት የምታቀርቡበት ብዙ መሠዊያዎችን ሠርታችኋል። 14ኤርምያስ ሆይ፥ እነርሱ በሚጨነቁበት ጊዜ ወደ እኔ ሲጮኹ ስለማልሰማቸው ለዚህ ሕዝብ አትጸልይ፤ ስለ እነርሱም ልመናና ምልጃ አታቅርብ።”
15እግዚአብሔር ለይሁዳ ሕዝብ እንዲህ እንድላቸው ነገረኝ፦ “እናንተ እኔ የምወዳችሁ ሕዝብ ናችሁ፤ ነገር ግን እንደእነዚህ ያሉ ክፉ ነገሮችን እያደረጋችሁ በዚህ በቤተ መቅደሴ ውስጥ ልትገኙ አይገባም፤ የምታቀርቡልኝም የእንስሶች መሥዋዕት ከጥፋት አይጠብቃችሁም፤ ስለዚህ በቤተ መቅደሴ ውስጥ መደሰታችሁን አቁሙ። 16አንድ ጊዜ እናንተ በፍሬ እንደ ተመላ የወይራ ዛፍ ነበራችሁ፤ ነገር ግን በቅርብ ጊዜ እንደ ነጐድጓድ የሚያስተጋባ ድምፅ በማሰማት ቅጠሉን በእሳት አቃጥላለሁ ቅርንጫፎችንም እሰባብራለሁ።
17“እኔ የሠራዊት አምላክ ነኝ፤ እናንተ የይሁዳና የእስራኤል ሕዝብ እኔ እንደ ተከልኩት ዛፍ ናችሁ፤ ነገር ግን በዓል ተብሎ ለሚጠራው ጣዖት መሥዋዕት በማቅረባችሁ አስቈጣችሁኝ፤ ስለዚህ አሁን ጥፋትን አመጣባችኋለሁ።”
ኤርምያስን ለመግደል የተደረገ ዐድማ
18በዚያን ጊዜ እነርሱ የሚያደርጉትን ነገር እግዚአብሔር ስላሳየኝ ሤራቸውን ዐወቅሁት። 19ወደ ዕርድ እንደሚሄድ የበግ ጠቦት ሆኜ ነበር፤ እነርሱ “ስሙ ዳግመኛ እንዳይታወስ ዛፉን ከነፍሬው እናጥፋ፤ ከሕያዋያን ዓለም እናስወግደው” ብለው በእኔ ላይ ማደማቸውን አላወቅሁም ነበር።
20እኔም እንዲህ በማለት ጸለይኩ፦ “የሠራዊት አምላክ ሆይ! የሰውን ልብና አእምሮ የምትመረምር አንተ ቅን ፈራጅ ነህ፤ እነሆ ችግሬን ለአንተ አስታወቅሁ፤ ስለዚህም በእነዚህ ሕዝብ ላይ የምትፈጽመውን በቀል እንዳይ አድርገኝ።”
21“በእግዚአብሔር ስም ትንቢት የተናገርክ እንደ ሆነ እንገድልሃለን” ብለው የኤርምያስን ሕይወት ለማጥፋት ስለሚፈልጉት ስለ አናቶት ሰዎች እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ 22“እኔ ራሴ እቀጣቸዋለሁ፤ ጐልማሶቻቸው በሰይፍ ያልቃሉ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውም በራብ ይሞታሉ። 23በዐናቶት ሕዝብ ላይ መቅሠፍት የማመጣበት ዘመን ሲደርስ ከእነርሱ መካከል አንድ ሰው እንኳ አይተርፍም።”
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 11: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997