መጽሐፈ መሳፍንት 7:9-17

መጽሐፈ መሳፍንት 7:9-17 አማ05

በዚያም ሌሊት እግዚአብሔር ጌዴዎንን እንዲህ አለው፥ “በእነርሱ ላይ ድልን እንድትቀዳጅ የማደርግህ ስለ ሆነ ተነሥተህ የእነርሱን ሰፈር አጥቃ። አንተ በሰፈሩ ላይ አደጋ ለመጣል ከፈራህ ግን ፑራ ተብሎ ከሚጠራው አገልጋይህ ጋር ወደ ሰፈሩ ውረድ፤ እነርሱም የሚሉትን ትሰማለህ፤ ከዚያም በኋላ በእነርሱ ላይ አደጋ ለመጣል ድፍረት ታገኛለህ፤”። ስለዚህ ጌዴዎንና አገልጋዩ ፑራ ወደ ጠላት ሰፈር ዳርቻ ወረዱ፤ ብዛታቸው እንደ አንበጣ መንጋ የሆነ ምድያማውያን፥ ዐማሌቃውያንና የምሥራቅ ሰዎች በሸለቆው ውስጥ ሰፍረው ነበር፤ ግመሎቻቸውም ከብዛታቸው የተነሣ እንደ ባሕር ዳር አሸዋ ሊቈጠር የማይቻል ነበር። ጌዴዎን እዚያ በደረሰ ጊዜ አንድ ሰው ያየውን ሕልም ለጓደኛው ሲነግረው ሰማ፤ ሕልሙም እንዲህ የሚል ነበር፦ “አንዲት የገብስ ቂጣ ከላይ ተንከባልላ ወርዳ ወደ ምድያም ሰፈር ደርሳ በዚያ ያለውን ድንኳን መታችው፤ ድንኳኑም ተገልብጦ በምድር ላይ ተዘረጋ።” ጓደኛውም “ይህማ የእስራኤላዊው የኢዮአስ ልጅ የጌዴዎን ሰይፍ ነው! ከቶ ሌላ ትርጒም ሊሰጠው አይችልም፤ እግዚአብሔር ለጌዴዎን በምድያምና በመላው ሠራዊታችን ላይ ድልን ሰጥቶታል!” ሲል መለሰለት። ጌዴዎን ስለ ሰውየው ሕልምና ስለ ፍቹም ምንነት በሰማ ጊዜ በጒልበቱ ተንበርክኮ ለእግዚአብሔር ሰገደ፤ ወደ እስራኤላውያንም ሰፈር ተመልሶ “እግዚአብሔር በምድያማውያንና በሠራዊቱ ላይ ድልን የሚያቀዳጃችሁ ስለ ሆነ ተነሡ!” አላቸው። ሦስት መቶዎቹንም ሰዎች ከፍሎ በሦስት ቡድን መደባቸው፤ ለእያንዳንዱም ሰው አንድ እምቢልታና በውስጡ ችቦ ያለበት አንድ ማሰሮ ሰጠ። እንዲህም አላቸው፤ “እኔ ወደ ሰፈሩ ዳርቻ ስደርስ፥ የማደርገውን በጥንቃቄ ተመልክታችሁ ያንኑ አድርጉ።