እግዚአብሔር ጌዴዎንን “በእጃቸው ውሃ እየዘገኑ በጠጡት በእነዚህ ሦስት መቶ ሰዎች አማካይነት አድናችኋለሁ፤ በምድያማውያን ላይ ድልን እንድትቀዳጅ አደርግሃለሁ፤ ለቀሩት ግን ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ንገራቸው” አለው። ስለዚህ ጌዴዎን የሕዝቡን ስንቅና እምቢልታዎቹን ከተረከቡት ከሦስት መቶዎቹ በቀር ሌሎቹን እስራኤላውያን ሁሉ ወደየቤታቸው እንዲመለሱ አሰናበታቸው፤ ይህም ሁሉ በሚሆንበት ጊዜ የምድያማውያን ሰፈር ከእነርሱ በታች በሸለቆው ውስጥ ነበር። በዚያም ሌሊት እግዚአብሔር ጌዴዎንን እንዲህ አለው፥ “በእነርሱ ላይ ድልን እንድትቀዳጅ የማደርግህ ስለ ሆነ ተነሥተህ የእነርሱን ሰፈር አጥቃ። አንተ በሰፈሩ ላይ አደጋ ለመጣል ከፈራህ ግን ፑራ ተብሎ ከሚጠራው አገልጋይህ ጋር ወደ ሰፈሩ ውረድ፤ እነርሱም የሚሉትን ትሰማለህ፤ ከዚያም በኋላ በእነርሱ ላይ አደጋ ለመጣል ድፍረት ታገኛለህ፤”። ስለዚህ ጌዴዎንና አገልጋዩ ፑራ ወደ ጠላት ሰፈር ዳርቻ ወረዱ፤ ብዛታቸው እንደ አንበጣ መንጋ የሆነ ምድያማውያን፥ ዐማሌቃውያንና የምሥራቅ ሰዎች በሸለቆው ውስጥ ሰፍረው ነበር፤ ግመሎቻቸውም ከብዛታቸው የተነሣ እንደ ባሕር ዳር አሸዋ ሊቈጠር የማይቻል ነበር። ጌዴዎን እዚያ በደረሰ ጊዜ አንድ ሰው ያየውን ሕልም ለጓደኛው ሲነግረው ሰማ፤ ሕልሙም እንዲህ የሚል ነበር፦ “አንዲት የገብስ ቂጣ ከላይ ተንከባልላ ወርዳ ወደ ምድያም ሰፈር ደርሳ በዚያ ያለውን ድንኳን መታችው፤ ድንኳኑም ተገልብጦ በምድር ላይ ተዘረጋ።” ጓደኛውም “ይህማ የእስራኤላዊው የኢዮአስ ልጅ የጌዴዎን ሰይፍ ነው! ከቶ ሌላ ትርጒም ሊሰጠው አይችልም፤ እግዚአብሔር ለጌዴዎን በምድያምና በመላው ሠራዊታችን ላይ ድልን ሰጥቶታል!” ሲል መለሰለት። ጌዴዎን ስለ ሰውየው ሕልምና ስለ ፍቹም ምንነት በሰማ ጊዜ በጒልበቱ ተንበርክኮ ለእግዚአብሔር ሰገደ፤ ወደ እስራኤላውያንም ሰፈር ተመልሶ “እግዚአብሔር በምድያማውያንና በሠራዊቱ ላይ ድልን የሚያቀዳጃችሁ ስለ ሆነ ተነሡ!” አላቸው። ሦስት መቶዎቹንም ሰዎች ከፍሎ በሦስት ቡድን መደባቸው፤ ለእያንዳንዱም ሰው አንድ እምቢልታና በውስጡ ችቦ ያለበት አንድ ማሰሮ ሰጠ። እንዲህም አላቸው፤ “እኔ ወደ ሰፈሩ ዳርቻ ስደርስ፥ የማደርገውን በጥንቃቄ ተመልክታችሁ ያንኑ አድርጉ። እኔና ከእኔ ጋር የተመደቡት ሰዎች በቀንደ መለከቶቻችን ድምፅ ስናሰማ፥ እናንተም የራሳችሁን እምቢልታ ድምፅ በሰፈሩ ዙሪያ እያሰማችሁ ‘ለእግዚአብሔርና ለጌዴዎን ተዋጉ!’ ብላችሁ ጩኹ።” ከእኩለሌሊት ጥቂት ቀደም ብሎ፥ ዘብ ጠባቂዎች ከተቀያየሩ በኋላ ጌዴዎንና ከእርሱ ጋር የተመደቡት መቶ ሰዎች ወደ ሰፈሩ ዳርቻ መጡ፤ እምቢልታዎቻቸውን ነፉ፤ የያዙትንም ማሰሮ ሁሉ ሰባበሩ። በሌላም በኩል የነበሩት ሁለቱ ክፍሎች እንዲሁ አደረጉ፤ ሁሉም የተለኰሱትን ችቦዎቻቸውን በግራ እጃቸው፥ እምቢልታቸውን በቀኝ እጃቸው ይዘው “ለእግዚአብሔርና ለጌዴዎን እንዋጋለን!” እያሉ በመጮኽ ደነፉ። እያንዳንዱ ሰው በሰፈሩ ዙሪያ በተመደበለት ቦታ ቆመ፤ መላው የጠላት ሠራዊትም የኡኡታ ድምፅ እያሰማ ሸሸ፤ ሦስት መቶው የጌዴዎን ሰዎች እምቢልታቸውን በሚነፉበት ጊዜ እግዚአብሔር እያንዳንዱን የጠላት ወታደር በጓደኛው ላይና በሠራዊቱ ላይ ሰይፉን እንዲያነሣ አደረገ፤ ሠራዊቱም ፊታቸውን ወደ ጽሬራ በመመለስ እስከ ቤትሺጣ፥ ከዚያም አልፎ በጣባት አጠገብ እስካለው አቤልመሖላ ድረስ ሸሽተው ሄዱ።
መጽሐፈ መሳፍንት 7 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ መሳፍንት 7:7-22
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos