መጽሐፈ መሳፍንት 15:1-12

መጽሐፈ መሳፍንት 15:1-12 አማ05

ከጥቂት ጊዜ በኋላ በስንዴ መከር ወራት ሶምሶን ሚስቱን ለመጐብኘት አንድ የፍየል ጠቦት ይዞ ሄደ፤ አባትዋንም “ሚስቴ ወዳለችበት ክፍል መግባት እፈልጋለሁ” አለው። አባትዋ ግን እንዲገባ አልፈቀደለትም፤ ሶምሶንንም “አንተ የጠላሃት ስለ መሰለኝ ሚዜህ ለነበረው ሰው ዳርኳት፤ የሆነ ሆኖ የእርስዋ ታናሽ ይበልጥ ውብ አይደለችምን? እባክህ እርስዋን አግባት” አለው። ሶምሶንም “ከእንግዲህ ወዲህ በፍልስጥኤማውያን ላይ ክፉ ነገር ባደርግ አልወቀስበትም!” አለ። ሄዶም ሦስት መቶ ቀበሮዎችን በማደን ያዘ፤ ጥንድ ጥንድ አድርጎ ጭራቸውን በማያያዝ በገመድ አሰረ፤ ችቦዎችም አምጥቶ በጭራቸው መካከል አሰረ። ከዚያም በኋላ በችቦዎቹ ላይ እሳት በማቀጣጠል ቀበሮዎቹን ገና ወዳልታጨደው ወደ ፍልስጥኤማውያን የስንዴ ሰብል ውስጥ ለቀቃቸው፤ በዚህም ዐይነት ታጭዶ የተከመረውን ብቻ ሳይሆን ገና በማሳ ላይ ያለውን ስንዴ፥ የወይራና የወይን ተክል ጭምር አቃጠለ። ፍልስጥኤማውያን ይህን ያደረገው ማን እንደሆን በጠየቁ ጊዜ፥ ሶምሶን መሆኑን ተረዱ፤ የቲምና ተወላጅ የሆነው ዐማቱ የሶምሶንን ሚስት ሚዜው ለነበረ ሌላ ሰው ሰጥቶበት ነበር፤ ስለዚህ ፍልስጥኤማውያን ሄደው ሴቲቱንና አባቷን በእሳት አቃጠሉ። ሶምሶንም “እንግዲህ እናንተ ይህን አድርጋችኋል፤ እኔ ደግሞ እናንተን ሳልበቀል አልተዋችሁም!” ብሎ ማለ። ወዲያውም ብርቱ አደጋ ጥሎባቸው ከእነርሱ ብዙዎችን ገደለ፤ ከዚህም በኋላ ሄዶ ዔጣም ተብላ በምትጠራ ስፍራ በዋሻ ውስጥ ተቀመጠ። ፍልስጥኤማውያን መጥተው በይሁዳ ሰፈሩ፤ ሌሒ ተብላ የምትጠራውንም ከተማ ወረሩአት፤ የይሁዳም ሰዎች “በእኛ ላይ አደጋ የምትጥሉት ስለምንድነው?” ሲሉ ጠየቁአቸው። እነርሱም “እኛ የመጣነው ሶምሶንን ልንይዝና እስረኛ አድርገን ወስደን በእኛ ላይ ያደረገውን ሁሉ በእርሱም ላይ ልንፈጽምበት ነው” ሲሉ መለሱላቸው። ስለዚህም ሦስት ሺህ የሚሆኑ የይሁዳ ሰዎች በዔጣም ወዳለው ዋሻ ሄደው “ፍልስጥኤማውያን ገዢዎቻችን እንደ ሆኑ አታውቅምን? ታዲያ ይህ ያደረግህብን ምንድን ነው?” ሲሉ ሶምሶንን ጠየቁት። እርሱም “እኔ በእነርሱ ላይ ያደረግኹት ልክ እነርሱ በእኔ ላይ ያደረጉትን ነው” አላቸው። እነርሱም “እኛ አሁን ወደዚህ የመጣነው አንተን አስረን ለእነርሱ አሳልፈን ልንሰጥህ ነው” አሉት። ሶምሶንም “እናንተ ራሳችሁ እንደማትገድሉኝ ማሉልኝ” አላቸው።