የያዕቆብ መልእክት 2:1-13

የያዕቆብ መልእክት 2:1-13 አማ05

ወንድሞቼ ሆይ! በክብር ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ የምታምኑ ከሆናችሁ አንዱ ከሌላው ይበልጣል በማለት በሰው መካከል አድልዎ አታድርጉ። ለምሳሌ ሁለት ሰዎች ወደምትሰበሰቡበት ቦታ ይመጣሉ፤ አንደኛው በጣቱ የወርቅ ቀለበት ያደረገና የሚያምር ጌጠኛ ልብስ የለበሰ ሀብታም ነው፤ ሌላው ያደፈ አሮጌ ልብስ የለበሰ ድኻ ነው፤ የሚያምር ጌጠኛ ልብስ የለበሰውን ሰው በማክበር “በዚህ በመልካሙ ቦታ ተቀመጥ” ትሉታላችሁ። ድኻውን ግን “አንተስ እዚያ ቁም፤ ወይም በእግሬ ሥር ተቀመጥ” ትሉታላችሁ፤ ታዲያ፥ በዚህ ዐይነት በመካከላችሁ ልዩነት እንደምታደርጉና የአድልዎ ፍርድ እንደምትፈርዱ አይታያችሁምን? የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ! ስሙ፤ እግዚአብሔር በእምነት ሀብታሞች እንዲሆኑና እርሱን ለሚወዱት ተስፋ የሰጣቸውን መንግሥት እንዲወርሱ የዚህን ዓለም ድኾች አልመረጠምን? እናንተ ግን ድኾችን ትንቃላችሁ፤ የሚጨቊኑአችሁና ወደ ፍርድ ቤት የሚጐትቷችሁስ ሀብታሞች አይደሉምን? እናንተ የምትጠሩበትን ያን ክቡር ስም የሚሰድቡስ እነርሱ አይደሉምን? “ሰውን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ” ተብሎ በቅዱስ መጽሐፍ የተጻፈውን የእግዚአብሔርን መንግሥት ሕግ ብትፈጽሙ መልካም ታደርጋላችሁ። በሰዎች መካከል ልዩነት ብታደርጉ ግን ኃጢአት ትሠራላችሁ፤ ሕግን በመተላለፋችሁም ትወቀሳላችሁ። ሰው ከትእዛዞች አንዱን አፍርሶ የቀሩትን ሁሉ ቢፈጽም እንኳ ሁሉንም እንዳፈረሰ ይቈጠራል። “አታመንዝር” ያለው ጌታ እንዲሁም “አትግደል” ብሎአል፤ ስለዚህ ባታመነዝርም እንኳ ከገደልክ ሕግን አፍርሰሃል። ነጻነትን በሚያስገኘው ሕግ ፊት ቀርበው እንደሚዳኙት ሰዎች ተናገሩ፤ እንዲሁም ሥሩ። የእግዚአብሔር ፍርድ ምሕረት ለማያደርግ ሰው ምሕረት አያደርግም፤ ሆኖም ምሕረት ፍርድን ያሸንፋል።